ኦሪት ዘኍልቍ 27
27
የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች ጥያቄ
1ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ወገን ፥ የምናሴ ልጅ፥ የማኪር ልጅ፥ የገለአድ ልጅ፥ የኦፌር ልጅ፥ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች መጡ፤ የእነዚህም ሴቶች ልጆች ስሞች መሐላ፥ ኑኃ፥ ሄግላ፥ ሚልካ፥ ቴርሳ ነበሩ። 2በምስክሩም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በሙሴና በካህኑ በአልዓዛር፥ በአለቆቹም፥ በማኅበሩም ሁሉ ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፦ 3“አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ በራሱ ኀጢአት ሞተ እንጂ ከቆሬ ጋር በእግዚአብሔር ላይ በተሰበሰቡ ወገን መካከል አልነበረም፤ ወንዶችም ልጆች አልነበሩትም። 4ወንድ ልጅስ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? 5በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስትን ስጠን።” ሙሴም ነገራቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ።
6እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 7“የሰለጰዓድ ልጆች እውነት ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ለእነርሱ ስጥ። 8ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ሰው ቢሞት፥ ወንድ ልጅም ባይኖረው፥ ርስቱን ለሴቶች ልጆቹ ትሰጣላችሁ፤ 9ሴት ልጅም ባትኖረው፥ ርስቱን ለወንድሞቹ ትሰጣላችሁ፤ 10ወንድሞችም ባይኖሩት፥ ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ትሰጣላችሁ፤ 11የአባቱም ወንድሞች ባይኖሩት ከወገኑ ለቀረበ ዘመድ ርስቱን ትሰጣላችሁ፤ እርሱም ይውረሰው፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ለእስራኤል ልጆች ሥርዐትና ፍርድ ይሁን።”
ኢያሱ በሙሴ ምትክ እንደ ተመረጠ
(ዘዳ. 31፥1-8)
12እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወደዚህ በናባው አሻገር ወዳለው ተራራ ውጣ፤ ለእስራኤልም ልጆች ይገዙአት ዘንድ እኔ የምሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እያት፤ 13ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ እንደ ተጨመረ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትጨመራለህ። 14እናንተ በጺን ምድረ በዳ በማኅበሩ ጠብ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አላከበራችሁኝምና። ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የክርክር ውኃ ነው።”
15ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 16“የሥጋና የነፍስ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የሚሆነውን ሰው ይሹም፤ 17በፊታቸው የሚወጣውንና የሚገባውን፥ የሚያስወጣቸውንና፥ የሚያስገባቸውንም፥ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን።” 18እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “መንፈስ ቅዱስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤ 19በካህኑም በአልዓዛር ፊት አቁመው፤ በማኅበሩም ፊት እዘዘው፤ ስለ እርሱም በፊታቸው እዘዝ። 20የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ ስጠው። 21በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፤ በቃሉም ይግቡ።” 22ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤ 23እግዚአብሔርም ሙሴን እንደ አዘዘው፥ እጁን በላዩ ጫነበትና፥ ሾመው፤ አዘዘውም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 27: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ