ኦሪት ዘኍልቍ 34
34
የተስፋይቱ ምድር ወሰኖች
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ እነሆ እናንተ ወደ ከነዓን ምድር ትገባላችሁ፤ የከነዓንም ምድር ከአውራጃዎችዋ ጋር ለእናንተ ርስት ትሆናለች። 3የአዜቡ ወገን ከጺን ምድረ በዳ በኤዶምያስ መያያዣ ይሆናል፤ የአዜብም ዳርቻ ከጨው ባሕር ዳር በምሥራቅ በኩል ይጀምራል፤ 4ዳርቻችሁም በአቅራቦን ዐቀበት በአዜብ በኩል ይዞራል፤ እስከ ኤናቅም ይደርሳል፤ መውጫውም በቃዴስ በርኔ በአዜብ በኩል ይሆናል፤ ወደ አራድ ሀገሮችም ይደርሳል፤ ወደ አሴሞናም ያልፋል፤ 5ዳርቻውም ከአሴሞና ወደ ግብፅ ወንዝ ይዞራል፤ ወሰኑ ባሕሩ ይሆናል።
6“ለባሕርም ዳርቻ ታላቁ ባሕር ዳርቻችሁ ይሆናል፤ ይህ የባሕር ዳርቻችሁ ይሆናል።
7“በመስዕም በኩል ወሰናችሁ ከታላቁ ባሕር በተራራው በኩል ይሆንላችኋል። 8ከተራራው እስከ ተራራው ድረስ ይሆንላችኋል፤ እስከ ኤማትም ይደርሳል፤ የዳርቻውም መውጫ በሰረደክ ይሆናል፤ 9ዳርቻውም ወደ ዲፍሮና ያልፋል፤ መውጫውም አርሴናይን ይሆናል፤ በመስዕ በኩል ያለው ወሰናችሁም በዚህ ይሁናችሁ።
10“በምሥራቅ በኩል ያለው ወሰናችሁም ከሴፋማ አርሴናይን#ዕብ. “ከአርሴናይን እስከ ሴፋማ” ይላል። ጀምሮ ነው። 11ዳርቻውም ከሴፋማ በዐይን ምሥራቅ ወዳለው ወደ አርቤላ ይወርዳል፤ እስከ ኬኔሬት የባሕር ወሽመጥ በምሥራቅ በኩል ይደርሳል፤ 12ዳርቻውም ወደ ዮርዳኖስ ይወርዳል፤ መውጫውም በጨው ባሕር ይሆናል። ምድራችሁ እንደ ዳርቻዋ በዙሪያዋ ይህች ናት።”
13ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፥ “እግዚአብሔር ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ይሰጡአቸው ዘንድ እንደ አዘዘ በዕጣ የምትወርሱአት ምድር ይህች ናት፤ 14የሮቤልም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የጋድም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ወርሰዋል። 15እነዚህ ሁለቱ ነገድና የአንዱ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ አንጻር በምሥራቅ በኩል ወረሱ።”
ምድሪቱን ለማከፋፈል ሐላፊነት የተሰጣቸው አለቆች
16እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ፤ ተናገረው፦ 17“ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚከፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ። 18ምድሪቱንም ርስት አድርገው የሚያካፍሏቸው ከየነገዱ አንድ አንድ አለቃ ይወስዳሉ። 19የሰዎቹም ስም ይህ ነው፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፥ 20ከስምዖን ልጆች ነገድ የዓሚሁድ ልጅ ሰላምያል፥ 21ከብንያም ነገድ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፥ 22ከዳን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዮቅሊ ልጅ ባቂ፥ 23ከዮሴፍም ልጆች ከምናሴ ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሱፊድ ልጅ አንሄል፥ 24ከኤፍሬም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሳፍጣን ልጅ ቃሙሔል፥ 25ከዛብሎን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የበርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፥ 26ከይሳኮር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሖዛ ልጅ ፈልጥሔል፥ 27ከአሴር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሴሌሚ ልጅ አኪሖር፥ 28ከንፍታሌም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የአሚሁድ ልጅ ፈዳሄል። 29እግዚአብሔር በከነዓን ምድር ለእስራኤል ልጆች ርስታቸውን ይከፍሉ ዘንድ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 34: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ