መጽሐፈ ምሳሌ 22
22
1መልካም ስም ከብዙ ባለ ጠግነት ይሻላል፥
መልካም ሞገስም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል።
2ባለ ጠጋና ድሃ በአንድነት ተገናኙ፤
ሁለቱንም እግዚአብሔር ፈጠራቸው።
3ዐዋቂ ሰው ክፉ ሰው በኀይል ሲቀጣ አይቶ ይገሠጻል፥
አላዋቂዎች ግን ሲያልፉ ይጐዳሉ።
4እግዚአብሔርን መፍራት፥
ጥበብን ባለጠግነትንና ክብርን፥ ሕይወትንም ትወልዳለች።
5እሾህና ወጥመድ በጠማማ ሰው መንገድ ናቸው፤
ነፍሱን የሚጠብቅ ግን ከእነርሱ ያመልጣል።
6ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥
በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።#በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በግእዝ የለም።
7ድሆች ባለጠጎችን ይገዛሉ፥
አገልጋዮችም ለጌቶቻቸው ያበድራሉ።
8ሐሰትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፥
የሥራውንም መቅሠፍት ይፈጽማል።
እግዚአብሔር ደስ ብሎት የሚሰጥ ሰውን ይወድዳል፥
ከንቱ ሥራውን ግን ይጠላል።
9ለድሃ የሚራራ እርሱ ይበላል
እንጀራውን ለድሃ ሰጥቶአልና።
ለሰጠው ሀብታምም የሚከፍል አይደለምና።#በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
መማለጃን የሰጠ ሰው ድል መንሣትንና ሞገስን ያገኛል፥
ነገር ግን የተቀበለውን ነፍስ ያጠፋል።
10ነፍሰ ገዳይን ከጉባኤ አውጣ፥ ከእርሱም ጋር ክርክር ይወጣል፥
በጉባኤ በሚቀመጥበት ጊዜ ሁሉን ያዋርዳልና።
11እግዚአብሔር የልብን የውሀት ይወድዳል።
ንጹሓንም ሁሉ በእርሱ ዘንድ የተመረጡ ናቸው።
ንጉሥ በከንፈሩ ይገዛል።
12የእግዚአብሔር ዐይኖች ዕውቀትን ይጠብቃሉ፤
ኃጥእ ግን የጥበብን ቃል ይንቃል።
13ታካች ሰው በላኩት ጊዜ ያመካኛል፥
እንዲህም ይላል፦ “አንበሳ በመንገድ አለ፥ በአደባባይም ግድያ አለ።”
14የዐመፀኛ አፍ ጥልቅ ጕድጓድ ነው፤
በእግዚአብሔርም ዘንድ የተጠላ በእርሱ ውስጥ ይወድቃል።
በሰው ፊት ክፉዎች መንገዶች አሉ፥
ከእነርሱም ይርቅ ዘንድ አይወድድም።
ከክፉና ከጠማማ መንገድም መራቅ አግባብ ነው።
15አለማወቅ የጐልማሳን ልብ ከፍ ከፍ አደረገች፤
በትርና ተግሣጽ ከእርሱ ርቀዋልና።
16ድሃን የሚቀማ ገንዘቡን ብዙ ያደርግለታል፥
በችግሩ ጊዜም ለባለጠጋ ይሰጣል።
17ለመስማት ጆሮህን ወደ ጠቢባን ቃል አዘንብል፥
የእኔንም ቃል ስማ፥ መልካምንም ታውቅ ዘንድ ልብህን አቅርብ።
18እነርሱን በልብህ ብትጠብቅ፥
በከንፈሮችህ በአንድነት ደስ ያሰኙሃል።
19ተስፋህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥
መንገዱን ያሳውቅሃል።
20ለዕውቀትና ለምክር ይሆኑህ ዘንድ ሦስት ነገሮችን እነሆ ጻፍሁልህ።
አንተም በልብህ ሰሌዳነት ጻፋቸው።
21በጎ ዕውቀትን ትሰማ ዘንድ፥ ለሚጠይቁህም የእውነት ቃልን ትመልስ ዘንድ
ነዋሪ ቃልን አስተምርሃለሁ።
22ድሃን በግድ አትበለው፥ ድሃ ነውና
ችግረኛውንም በበር አትግፋው፤
23እግዚአብሔር ፍርዱን ይፈርድለታልና።
አንተም ነፍስህን በሰላም ታድናለህ።
24ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥
ከነዝናዛም ጓደኛ ጋር አትኑር።
25መንገዱን እንዳትማር፥
ለነፍስህም ወጥመድ እንዳያገኝህ።
26የሰውን ፊት በማፈር ራስህን ለዋስትና አትስጥ።
27የምትከፍለው ባይኖርህ፥
ምንጣፍህን ከጎንህ ይወስዱብሃልና።
28አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን ድንበር አታፍርስ።
29ነገርን የሚረዳ፥ በሥራውም ብልህ የሆነ ሰው፥
ወደ ነገሥታት ይቀርባል፤
በተዋረዱ ሰዎችም ፊት አይቆምም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 22: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ