መዝሙረ ዳዊት 71
71
ስለ ሰሎሞን።
1አቤቱ፥ ፍርድህን ለንጉሥ ስጠው፥
ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ፥
2ሕዝብህን በጽድቅ፥
ድሆችህንም በፍርድ ይዳኝ ዘንድ።
3ተራሮችና ኮረብቶች የሕዝብህን ሰላም ይቀበሉ።
4ለድሆች ሕዝብህ በጽድቅ ፍረድ፥
የድሆችንም ልጆች አድናቸው።
ትዕቢተኛውንም አዋርደው።
5ፀሐይ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ፥
በጨረቃም ፊት ለልጅ ልጅ ይኑር።
6እንደ ጠል በባዘቶ ላይ፥
በምድርም ላይ እንደሚንጠባጠብ ጠብታ ይወርዳል።
7በዘመኑም ጽድቅ ይበቅላል፥
ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው።
8ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፥
ከወንዝም እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ይገዛል።
9በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥
ጠላቶቹም አፈርን ይልሳሉ።
10የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤
የሳባና የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያመጣሉ፤
11የምድር ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል ፥
አሕዛብም ሁሉ ይገዙለታል።
12ድሃውን ከሚቀማው እጅ፥
ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና።
13ለድሃና ለምስኪን ይራራል፥
የድሆችንም ነፍስ ያድናል።
14ከአራጣና ከቅሚያ ነፍሳቸውን ያድናታል፤
ስሙም በፊታቸው ክቡር ነው።
15እርሱ ይኖራል፥ ከዓረብም ወርቅን ይሰጡታል፤
ሁልጊዜም ስለ እርሱ ይጸልያሉ፥
ዘወትርም ይመርቁታል።
16በተራሮች ራስ ላይ ለምድር ሁሉ መጠጊያ ይሆናል፤
ፍሬውም ከሊባኖስ ዛፍ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፤
እንደ ምድር ሣር በከተማ ይበቅላል።
17ስሙ ለዘለዓለም ቡሩክ ነው፥
ከፀሓይም አስቀድሞ ስሙ ነበረ፤
የምድር አሕዛብ ሁሉ በእርሱ ይባረካሉ፥
ሕዝቡ ሁሉ ያመሰግኑታል።
18ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን።
19የምስጋናው ስም ለዓለምና ለዘለዓለም ይባረክ፤
ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይምላ።
ይሁን፤ ይሁን።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “የእሴይ ልጅ የዳዊት መዝሙር ተፈጸመ” የሚል ይጨምራሉ።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 71: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ