መዝሙረ ዳዊት 73
73
የአሳፍ ትምህርት።
1አቤቱ፥ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸን?
በማሰማሪያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ለምን ተቈጣህ?
2አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥
የተቤዠሃትንም የርስትህን በትር፥
በውስጥዋ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ ዐስብ።
3ጠላት በቅዱሳንህ ላይ እንደ ከፋ መጠን፥
ሁልጊዜ በትዕቢታቸው ላይ እጅህን አንሣ።
4ጠላቶችህ በበዓልህ መካከል ተመኩ፤
የማያውቁትንም ምልክት ምልክታቸው አደረጉ።
5እንደ ላይኛው መንገድ፥
በዱር እንዳሉም እንጨቶች፥
በገጀሞ በሮችዋን ሰበሩ።
6እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት።
7መቅደስህንም በእሳት አቃጠሉ፤
የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ።
8አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው አሉ፦
“ኑ፥ የእግዚአብሔርን በዓላት ከምድር እንሻር
9ምልክቱንም አናውቅም፥#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ምልክታችንንም አናይም” ይላል። ከእንግዲህ ወዲህ ነቢይ የለም፤
እኛም ከእንግዲህ ወዲህ አናውቅም።”#ከዕብራይስጥና ከግሪክ ሰባ. ሊ. ይለያል።
10አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል?
ስምህንስ ጠላት ሁልጊዜ ያስቈጣዋል?
11አቤቱ፥ እጅህን ፈጽመህ ለምን ትመልሳለህ?
ቀኝህንም በብብትህ መካከል፥
12እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥
በምድርም መካከል መድኀኒትን አደረገ።
13አንተ ባሕርን በኀይልህ አጸናሃት፤
አንተ የእባቡን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ።
14አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤
ለኢትዮጵያ ሕዝብም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።#ዕብ. “ለምድረ በዳ ሰዎች” ሲል ግሪክ ሰባ. ሊ. “እርሱንም ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግብ አድርገህ ሰጠሃቸው” ይላል።
15አንተ ፈሳሾቹንና ምንጮቹን ሰነጠቅህ።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “አንተ የኤታምን ወንዞች አደረቅህ” የሚል ይጨምራል።
16ቀኑ የአንተ ነው፥ ሌሊቱም የአንተ ነው፤
አንተ ፀሐይንና ጨረቃን ፈጠርህ።
17አንተ የምድር ዳርቻዎችን ሁሉ ሠራህ፤
በጋንና ክረምትን አንተ አደረግህ።
18ይህን ፍጥረትህን ዐስብ።
ጠላት እግዚአብሔርን ተገዳደረው።
ሰነፍ ሕዝብም ስሙን አስቈጣ።
19የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት፤
የድሆችህንም ነፍስ ለዘወትር አትርሳ።
20ወደ ኪዳንህም ተመልከት፥
የምድር የጨለማ ስፍራዎች በኃጥኣን ቤቶች ተሞልተዋልና።
21ችግረኛ አፍሮ አይመለስ፤
ድሃና ምስኪን ስምህን ያመሰግናሉ።
22አቤቱ፥ ተነሥ፥ በቀሌንም ተበቀል፤
ሰነፎች ሁልጊዜ የተገዳደሩህን ዐስብ።
23የባሪያዎችህን ቃል አትርሳ፤
የጠላቶችህ ኵራት ሁልጊዜ ወደ አንተ ይውጣ።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 73: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ