መጽሐፈ ተግሣጽ 1
1
1 # ምዕ. 1 በዕብራይስጥ እና በግሪክ ሰባ. ሊ. ምሳሌ ምዕ. 25 ነው። የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ወዳጆች ያለ ጥርጥር የጻፉት የተለያየ የሰሎሞን ተግሣጽ ነው።
2የእግዚአብሔር ክብር ነገርን ይሰውራል፥
የንጉሥ ክብር ግን ነገርን ያከብራል።
3ሰማይ ከፍ ያለ ነው፥ ምድርም ጥልቅ ነው፥
የንጉሥ ልብም እንዲሁ አይታወቅም።
4ያልጠራውን ብር አጥራው፥
ፈጽሞም ይጠራል።
5ከንጉሡ ፊት ክፉዎችን አጥፋ፥
ዙፋኑም በጽድቅ ይቀናል።
6በንጉሥ ፊት አትታበይ፥
በእግዚአብሔርም ፊት አትመጻደቅ፥#“በእግዚአብሔርም ፊት አትመጻደቅ” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
በመኳንንት ስፍራ አትቁም፤
7በመኰንን ፊት ከምቷረድ፦
ወደዚህ ከፍ በል ብትባል ይሻልሃልና፥
ዐይኖችህ ያዩትን ተናገር።
8ኋላ እንዳትጸጸት፥
ለጥል ፈጥነህ አትውጣ።
ክርክርን ከባልንጀራህ ጋር ተከራከር፥
ምሥጢሩንም አትግለጥ።
9ባልንጀራህ በነቀፈህ ጊዜ ወደኋላህ ተመለስ፥
ባልንጀራህም እንዳይነቅፍህ ቸል አትበለው፥
ጠብህም ክርክርህም ከእርሱ አያርቅህም።
10ምሥጢሩን ብትገልጥ ግን የሞት ያህል ይሆንብሃል፥
ጸጋና ወንድማማችነትም ነጻ ያደርጋል።
ነገር ግን መዘባበቻ እንዳትሆን ራስህን ጠብቅ፤
በመልካም ሥራህም መንገዶችህን ጠብቅ።
11በብር ጻሕል ላይ ያለ የወርቅ ዕንኰይ ያማረ እንደሚሆን፥
በየመልኩ የሚናገሩት ቃልም እንዲሁ ነው።
12በወርቅ ጉትቻ ላይ ያለ ዋጋው ብዙ የሆነ ሰርድዮን የሚባል የዕንቍ ፈርጥ ያማረ እንደሆነ፥
እንደዚሁ የብልህ ነገር በሚሰማ ሰው ጆሮ ያማረ ነው።
13በመከር ወራት በቈላ የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ፥
እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ይጠቅማል።
የጌቶቹን ነፍስ ያሳርፋልና።
14በሐሰተኛ ሀብት የሚመኩ ሁሉ፥
ዝናብ እንደሌላቸው ደመናትና ነፋሳት ናቸው።
15የሕይወት ውበት በትዕግሥት ትነግሣለች፥#ዕብ. “በትዕግሥት አለቃ ይለዝባል” ይላል።
ልዝብ አንደበትም አጥንትን ትሰብራለች።
16ልጄ ሆይ፥ አጥብቀህ እንዳትጠግብ፥ እንዳትተፋውም
ማር ባገኘህ ጊዜ በልኩ ብላ።
17እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም፥
እግርህን ወደ ባልጀራህ ቤት አታዘውትር።
18በባልጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር፥
እንደ በትርና እንደ ሰይፍ እንደ ተሳለም ፍላጻ ነው።
19የክፉ መንገድና የኀጢአተኛ እግር፥
በክፉ ቀን ይጠፋሉ።
20መጻጻ ለቍስል እንደማይመች፥
እንደዚሁም በሥጋ ላይ የሚወርድ ነውር ልብን ያሳዝናል።
ነቀዝ ዕንጨትን፥ ብልም ልብስን እንደሚበላው፥
እንደዚሁ ኀዘን የሰውን ልብ ትጐዳለች።
21ጠላትህ ቢራብ አብላው፥
ቢጠማም አጠጣው።
22ይህን ብታደርግ በራሱ ላይ ፍም ትሰበስባለህ፥
እግዚአብሔርም መልካም ዋጋህን ይመልስልሃል።
23የሰሜን ነፋስ ወጀብ ያመጣል፤
ፊትን የማያፍር ምላስም ያስቈጣል።
24ከነዝናዛ ሴት ጋር ባማረ ቤት ከመቀመጥ፥
አንድ ጎኑ በፈረሰ ግንብ መቀመጥ ይሻላል።
25የቀዘቀዘ ውኃ ለተጠማች ሰውነት መልካም እንደ ሆነ፥
ከሩቅ ሀገር የመጣ የምሥራችም እንዲሁ መልካም ነው።
26በኃጥኣን ፊት የጻድቅ መውደቅ፥
ጕድጓድን እንደ መዝጋትና የውኃ መውጫን እንደ ማጥፋት ነው።
27ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፤
እንዲሁም የራስን ክብር መፈለግ አያስከብርም።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የከበረውን ቃል ማክበር ይገባል” ይላል።
28ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፥
ያለ ምክር የሚኖር ሰው እንዲሁ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ተግሣጽ 1: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ