መጽሐፈ ተግሣጽ 2
2
1 # በዕብራይስጥና በግሪክ ሰባ. ሊ. ምሳሌ ምዕ. 26 ነው። ጠል በመከር ዝናምም በበጋ ጥቅም እንደሌለው፥
እንዲሁ ለሰነፍ ክብር አይገባውም።
2እንደሚተላለፍ ድንቢጥ፥ ወዲያና ወዲህም እንደሚበርር ጨረባ፥
እንዲሁ ከንቱ ርግማን በማንም ላይ አይደርስም።
3አለንጋ ለፈረስ፥ መውጊያ ለአህያ እንደ ሆነ፥
እንደዚሁም በትር ለሰነፍ ጀርባ ነው።
4ልጄ ሆይ፥ አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል፥
ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት።
5ነገር ግን ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው፥
ለሰነፍ እንደ ስንፍናው መልስለት።
6በሰነፍ መልእክተኛ እጅ ነገርን የሚልክ፥
በእግሮቹ ውርደትን ያመጣል።
7የአንካሳ እግሮች አካሄድ ልዩ ነው፥
እንዲሁም በደል በሰነፎች አፍ ነው።
8ለሰነፍ ክብርን የሚሰጥ
ድንጋይን በወንጭፍ እንደሚያስር ነው።
9እሾህ በሰካራም እጅ እንደሚሰካ፥
እንዲሁም መገዛት በሰነፎች እጅ ነው።
10የአላዋቂ ሰውነት ሁሉ ብዙ ይታወካል፥
ዐሳቡ ይበታተናልና።#ከዕብ. በብዛት ይለያያል።
11ወደ ትፋቱ የሚመለስ ውሻ የተጠላ እንደሆነ
በክፋቱ ወደ ኀጢአቱ የሚመለስ አላዋቂም እንዲሁ ነው።
ኀጢአትን የምታመጣ ኀፍረት አለች፤
ክብርንና ጸጋን የሚያመጣ ኀፍረትም አለ።
12ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚመስለውን ሰው አየሁ፥
ከእርሱ ይልቅ ለአላዋቂ እጅግ ተስፋ አለው።
13ታካች ሰው በላኩት ጊዜ፥ “አንበሳ በመንገድ አለ፤
በሜዳም ገዳዮች አሉ” ይላል።
14ሣንቃ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፥
እንዲሁ ታካች ሰው በአልጋው ላይ ይመላለሳል።
15ታካች ሰው እጁን በብብቱ ይሸሽጋል፤
ወደ አፉም ይመልሳት ዘንድ ለእርሱ ድካም ነው።
16ታካች ሰው መልእክትን በአጥጋቢ ሁኔታ ከሚመልስ ሰው ይልቅ፥
ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል።
17አልፎ በሌላው ጥል የሚደባለቅ፥
የውሻን ጅራት እንደሚይዝ ነው።
18ይድኑ ዘንድ የሚወድዱ ለሰው ነገርን እንደሚያወጡ
እንደዚሁ ነገርን የሚቀበል አስቀድሞ ይወድቃል፥
19ባልንጀራቸውን የሚያታልሉ ሁሉ እንደዚሁ ናቸው፤
ካወቁባቸውም በኋላ በጨዋታ አደረግነው ይላሉ።
20በዕንጨት መታጣት እሳት ይጠፋል፥#“በዕንጨት መታጣት እሳት ይጠፋል” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
በዕንጨት ብዛትም እሳት ይነድዳል፥
ቍጡ በሌለበትም ዘንድ ጠብ ጸጥ ይላል።
21ከሰል ፍምን፥ ዕንጨትም እሳትን እንዲያበዛ፥
እንዲሁ ተሳዳቢ ሰው ለጠብና ለክርክር ነው።
22የአታላዮች ቃል ደካማ ነው፥
ነገር ግን የምሕረት መዝገቦችን ይሰብራል።
23በሐሰት የሚሰጥ ብር እንደ ገል ነው፥
በሸክላ ዕቃ ላይ የሚለበጥ ብር ግብዝ እንደ ሆነ#በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
እንደዚሁም ልዝቦች ከንፈሮች ያዘነች ልብን ይሸፍናሉ።
24ጠላት እያለቀሰ በከንፈሩ ተስፋ ይሰጣል፥
በልቡ ግን ተንኮልን ያኖራል።
25ጠላትህ በታላቅ ድምፅ ደስ ቢያሰኝህ አትመነው፥
በልቡ ሰባት ክፋቶች አሉበትና።
26ጠላትነቱን የሚሸሽግ ተንኰልን ይሰበስባል፥
ዐዋቂ ግን በጉባኤ መካከል በደሉን ይገልጣል።
27ጕድጓድን ለባልንጀራው የሚምስ ራሱ ይወድቅበታል፥
ድንጋይንም የሚያንከባልል በላዩ ይገለበጥበታል።
28ሐሰተኛ ምላስ እውነትን ትጠላለች፥
ዝም የማይል አፍም ክርክርን ያመጣል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ተግሣጽ 2: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ