መጽሐፈ ተግሣጽ 4
4
1 # በዕብራይስጥና በግሪክ ሰባ. ሊ. ምሳሌ ምዕ. 28 ነው። ኃጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤
ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ተማምኖ ይኖራል።
2በክፉዎች በደል መቅሠፍት ይነሣል፤
ዐዋቂ ሰው ግን ፈጽሞ ያጠፋዋል።
3በኀጢአት የጸና ሰው ድሆችን ይቀማል፤
እንደማይጠቅም እንደ ከባድ ዝናብም ነው፥
4ሕግን የሚተዉና ኀጢአትን የሚያወድሱ እንደዚሁ ናቸው።
ሕግ ጠባቂዎች ግን ለራሳቸው ቅጥርን ይሠራሉ።
5ክፉዎች ሰዎች ፍርድን አያስተውሉም፤
እግዚአብሔርን የሚሹ ግን ሁሉን ያስተውላሉ።
6ከሐሰተኛ ባለጠጋ፥
በእውነት የሚሄድ ድሃ ይሻላል።
7ሕግን የሚጠብቅ ልጅ ዐዋቂ ነው፤
አመንዝራ ሴትን የሚመለከት ግን ለጥፋት ይዳረጋል፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለጥፋት ይዳረጋል” አይልም።
አባቱንም ያሰድባል።
8በአራጣና በቅሚያ ሀብቱን የሚያበዛ
ለድሃ ለሚራራ ያከማችለታል።
9ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ሰው
ጸሎቱ የተናቀ ነው።
10ቅኖችን#አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ዕውራንን” ይላል። በክፉ መንገድ የሚያስት፥
እርሱ ወደ ጥፋት ይወድቃል፤
ዐመፀኞች ግን በመልካም በኩል ያልፋሉ፥
ወደ ውስጧም አይገቡም።
11ባለጠጋ ሰው ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል፤
አስተዋይ ድሃ ግን ይመረምረዋል።
12በጻድቃን ረድኤት ብዙ ክብር አለ፤
በኃጥኣን መንገድ ግን ሰዎች ይጠፋሉ።
13በደሉን የሚሰውር ሰው መንገዱ አይቃናም፤
የሚናዘዝና ራሱን የሚዘልፍ ግን ይወደዳል።
14ስለ ጽድቅ ሁልጊዜ የሚደነግጥ ሰው ብፁዕ ነው፤
ልቡን የሚያጸና ግን በክፉ ይወድቃል።
15ራሱ ድሃ ሆኖ ሳለ ድሃ ሕዝብን የሚያስጨንቅ ክፉ መኰንን፥
እንደ ተራበ አንበሳና እንደ ተጠማ ተኵላ ነው።
16አእምሮ የጐደለው ንጉሥ ብዙ ግብርን አስገባሪ ይሆናል፤
ግፍን የሚጠላ ግን ብዙ ዘመን ይኖራል።
17በሰው ደም የሚገባ ዐመፀኛ ሰው
ወደ ጕድጓድ በሚገባበት ጊዜ የሚይዘው የለም፥#“በሰው ደም የሚገባ ዐመፀኛ ሰው ወደ ጕድጓድ በሚገባበት ጊዜ የሚይዘው የለም” የሚለውን ግእዙ ከዕብራይስጡ የወሰደው ነው።
ለነፍሰ ገዳይም ዋስ የሚሆን ሰው ይሰደዳል፥
በደኅናም አይኖርም።
ልጅህን አስተምረው ይወድድሃልም፥
ለነፍስህም ክብርን ይሰጣል።
ዐመፀኛ ሕዝብ ሕግን አይሰማም።#በዕብራይስጥ የለም።
18በጽድቅ መንገድ የሚሄድ ሰው ይረዳል፥
በጠማማ መንገድ የሚሄድ ግን በወጥመድ ይያዛል።
19ምድሩን የሚያርስ እንጀራን ይጠግባል፤
ሥራ ፈትነትን የሚያበዛ ግን ድህነትን ያበዛል።
20የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤
ክፉ ሰው ግን ከቅጣት አይድንም።
21የጻድቃንን ፊት የማያፍር ሰው ደግ አይደለም፥
እንዲህ ያለ ሰው በቍራሽ እንጀራ ሰውን አሳልፎ ይሰጣል።
22ምቀኛ ሰው ባለጠጋ ለመሆን ይቸኩላል፥
የሚራራ ሰውም እንደሚገዛው አያውቅም።
23በምላሱ ከሚሸነግል ሰው ይልቅ
የሰውን መንገድ የሚነቅፍ እጅግ ክብርን ያገኛል።
24ከአባቱና ከእናቱ የሚሰርቅ፥
ኀጢአትንም አልሠራሁም የሚል፥
የአጥፊ ባልንጀራ ነው።
25የሚሳሳ ሰው ከንቱን ይፈርዳል፤
በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በጥንቃቄ ይኖራል።
26በልቡ ደስታ የሚታመን ሰው እንደዚሁ ሰነፍ ነው፤
በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል።
27ለድሃ የሚሰጥ አይቸገርም፤
ዐይኖቹን የሚያዞር ግን በከባድ ችግር ይኖራል።
28በኃጥኣን ቦታ ጻድቃን ያለቅሳሉ፥
በእነርሱ ጥፋት ግን ጻድቃን ይበዛሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ተግሣጽ 4: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ