መጽሐፈ ሲራክ 44
44
የቀደሙ አባቶች ውዳሴ
1የከበሩ ሰዎችንና አባቶቻችንን በዘመናቸው እናመስግናቸው።
2እግዚአብሔር ብዙ ክብርን ሰጥቶአቸዋልና፥
ከመጀመሪያ ጀምሮ አግንኖአቸዋልና።
3በኀይላቸው ስማቸውን ያስጠሩ፥ በጥበባቸው የሚመክሩ፥
ትንቢትንም የሚናገሩ ሰዎች በመንግሥታቸው ገዙ።
4የአሕዛብ ነገሥታት በሰልፋቸው፥
የሕዝቡም ጸሓፊዎች በምክራቸው፥ በልባቸውም ባለ በቃላቸው ጥበብ፤
5ምስጋናንና ያማረ መሰንቆን የሚፈልጉ፥
በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ አድርገው የሚያመሰግኑ፥
6ባለጸጎች የሆኑ ገንዘባቸው የሚበቃቸው፥
በቤታቸው በደኅና የሚኖሩ ሰዎችም፤
7እነዚህ ሁሉ በዘመናቸው የከበሩ፥
በሕይወታቸውም የተዘጋጁ ናቸው፤
8ከእነርሱም ውዳሴያቸው ይነገር ዘንድ፥
የከበረ ስምን የተዉ አሉ።
9የሚያስባቸው የሌለ፥ የጠፉም፥
እንዳልተፈጠሩና እንዳልተወለዱ የሆኑም አሉ።
ልጆቻቸውም ከእነርሱ ጋራ እንደ እነርሱ ጠፉ።
10እነዚህ ግን ጽድቃቸው ያልተዘነጋችባቸው፥
ይቅርታን የተሞሉ ናቸው፤
11ያማረች ርስታቸውም ከልጆቻቸው ጋራ ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች።
ልጆቻቸውም በሥርዐታቸው ይኖራሉ።
12ዘራቸው ፈጥኖ ይቆማል፥
ልጆቻቸውም በእነርሱ ፋንታ ናቸው፤
13ዘራቸውም ለዘለዓለም ይኖራል፤
ክብራቸውም አያልቅም።
14ሥጋቸውም በሰላም ተቀበረ፤
ስማቸውም ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች።
15አሕዛብም ጥበባቸውን ይናገራሉ፤
በአሕዛብም ሸንጎ ያመሰግኗቸዋል።
ስለ ሄኖክና ኖኅ
16ሄኖክ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤
እግዚአብሔርም እርሱን ሰወረው፤
ንስሓም ይገቡ ዘንድ ለትውልድ ሁሉ አብነት ሆነ።
17ኖኅም ፍጹምና ጻድቅ ሆኖ ተገኘ፤
በጥፋትም ዘመን እርሱ ለዓለም ምክንያት ሆነ፤
የጥፋትም ውኃ በወረደ ጊዜ እርሱ ለምድር ዘር ሆኖ ቀረ።
18የጥፋት ውኃ ሰውን ሁሉ እንዳያጠፋው፥
እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ለዘለዓለሙ ቃል ኪዳን አደረገ።
ስለ አብርሃም
19የአሕዛብ ሁሉ አባት አብርሃም ታላቅ ነው፤
የልዑልን ሕግ የጠበቀ፥ ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳን ያደረገ፥
በክብር እርሱን የሚመስል አልተገኘም።
20እግዚአብሔርም በሰውነቱ ቃል ኪዳንን አጸናለት።
በፈተነውም ጊዜ የታመነ ሆኖ ተገኘ።
21ስለዚህም አሕዛብ በዘሩ ይባረኩ ዘንድ፥
እንደ ባሕር አሸዋም ያበዛቸው ዘንድ፥
ዘሩም እንደ ሰማይ ከዋክብት ይበዙ ዘንድ፥
ከባሕር እስከ ባሕርም ድረስ ያወርሳቸው ዘንድ፥
ከወንዞችም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ያወርሳቸው ዘንድ ቃል ኪዳንን አጸናለት፥
ይስሐቅና ያዕቆብ
22ለይስሐቅም ስለ አባቱ ስለ አብርሃም ደግነት፥
ለሰው ሁሉ የምትሆን በረከትንና ቃል ኪዳንን አጸናለት።
23በያዕቆብ ራስ ላይም ዐረፈች፥
በረከቱም ተገለጠችለት፥
እርሷንም ርስት አድርጎ ሰጠው፤ ርስታቸውንም በየወገናቸው ለየላቸው፥
ለዐሥራ ሁለቱ ነገድም ርስታቸውን ከፈለላቸው።
24ከእነርሱም የከበሩና በሰው ዘንድ ሞገስን ያገኙ፥
በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድም የተወደዱ ጻድቃን ሰዎችን አስነሣ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከእርሱ የከበረና በሰው ዘንድ ሞገስን ያገኘ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ የተወደደ ሰውን አስነሣ” ይላል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 44: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ