መጽሐፈ ሲራክ 45
45
ሙሴ
1ሙሴም ስም አጠራሩ የተባረከ ነው፤
መታሰቢያውና አምሳሉም እንደ ቅዱሳን ክብር ነው።
2ከፍ ከፍም አደረገው፤
በጠላቶቹም ላይ የሚያስፈራ ሆነ።
3በቃሉም ተአምራትን አደረገ፤
በነገሥታቱም ፊት አከበረው፤
ስለ ሕዝቡም አዘዘው፤ ክብሩንም አሳየው።
4ስለ ሃይማኖቱና ስለ የዋህነቱም ቀደሰው፤
ከሰውም ሁሉ እርሱን መረጠው።
5ቃሉንም አሰማው፤
ወደ ደመናውም ውስጥ አገባው፤
ትእዛዙንም በፊቱ ሰጠው፤
ለያዕቆብ ቃል ኪዳኑን፥ ለእስራኤልም ፍርዱን ያስተምር ዘንድ የሕይወት ሕግን ሰጠው።
አሮን
6ከሌዊ ወገን የተወለደ ወንድሙ አሮንም እንደ እርሱ ታላቅ ነው፤
ቅዱስም፥ የከበረም ነው።
7የዘለዓለም ሕግንም አጸናለት፤
በሕዝቡም መካከል ክህነትን ሰጠው፤
በአማረ ጌጥም አስደነቀው፤
የክብር ልብስንም አለበሰው።
8በሁሉም ዘንድ አስመካው፤
በከበሩ ልብሶችም አጸናው፤
እጀ ሰፊና እጀ ጠባብንም፥ ኤፉድንም አለበሰው።
9በዙሪያውም ብዙ ሮማንና የወርቅ ጸናጽል አለ፤
በእግሩም በረገጠ ጊዜ የመርገፉ ድምፅ በቤተ መቅደስ ይሰማ ዘንድ ይጮህ ነበር፤
ይህም ለሕዝቡና ለልጆቻቸው መታሰቢያ ሆነ።
10የተለየ ሰማያዊ ሐር ያለበት አራት ኅብርን፥
አምስተኛ ወርቀ ዘቦ ያለበት በነጭ ሐር የተሠራ ልብስንም፥
በሚገባና በእውነት ነገር የተሠራ ልብሰ መትከፍ አለበሰው።
11የነጭ ሐር የሚሆን ፈትሉ እጥፍ የሆነ፥
ዕንቍም ያለበት፥
የማኅተምም ቅርጽ ያለበት ልብስን በልብስ ላይ አለበሰው፤
እጀ ጠባቡም በወርቅ የተሠራ ነው፤
በየወገናቸው መታሰቢያ ሊሆን በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልጆች ቍጥር ልክ የተጻፈ ነው።
12በማኅተም መልክ አምሳል የተሠራ የወርቅ አክሊልን
በዝግራ መጠምጠሚያው ላይ አደረገለት፤
የተለየ የክብሩ መመኪያ የሚሆን ተአምራት የሚያደርግበት፥
ለዐይን የተወደደ፥ ጌጡ ፈጽሞ ያማረ የወርቅ መጠምጠሚያን በዝግራ መጠምጠሚያው ላይ አደረገለት።
13ከእርሱ አስቀድሞ እንደ እርሱ ልብስ ያለ ልብስ አልተሠራም፤
ከልጆቹ ብቻ በቀር፥ ለዘለዓለም ከዘመዶቹም በቀር እንደ እርሱ የለበሰ የለም።
14ሁልጊዜ በየዕለቱ የጧትና የማታ መሥዋዕት ይሠዉለት ዘንድ፥
15ሙሴም እጃቸውን ቀባላቸው፤
የተቀደሰውንም ዘይት ቀባው፤
ለዘለዓለሙም ሕግ ሆነው፤ ይገዙለት ዘንድ፤ ካህናትም ይሆኑት ዘንድ፤ ሕዝቡንም በስሙ ይባርኳቸው ዘንድ፤
ሰማይ ጸንቶ በሚኖርበት ዘመን ልክ ለልጆቹ ሕግ ሆናቸው።
16ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ይሠዋ ዘንድ፥
የበጎ መዓዛ መታሰቢያም ሊሆን ዕጣንን ያጥን ዘንድ፥
ለሕዝቡም ኀጢአታቸውን ያስተሰርይላቸው ዘንድ ከሕያዋን ሁሉ እርሱን መረጠ።
17ትእዛዛቱን ሰጠው፤
ለያዕቆብ ምስክሩን ያስተምረው፥
ለእስራኤልም ሕጉን ያስተምረው ዘንድ ፍርድንና ሥልጣንን ሰጠው።
18ሌሎች ግን ተቃወሙት፤
የዳታንና የአቤሮን የሆኑ ሰዎች፥ የእነቆሬም ሠራዊት
በመናደድና በመቈጣት በምድረ በዳ ቀኑበት።
19እግዚአብሔርም አያቸው፤ ደስም አላሰኙትም፤
ተቈጥቶም አጠፋቸው፤
በእነርሱም ላይ ድንቅ ተአምራትን አደረገ፤
በእሳትም አጠፋቸው።
20ለአሮንም ክብርን ጨመረለት፤
የእህላቸውንም ቀዳምያት ዕድል ፋንታ አድርጎ ሰጠው።
21ለእርሱና ለልጆቹም የሰጣቸውን የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ይበሉ ዘንድ፥
የሚያጠግባቸው ዐሥራቱን አስቀድሞ ሠራላቸው።
22የሕዝቡንም ምድር አልተካፈለም፤
ከሕዝቡም ጋራ ርስትን አልወረሰም፤
እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ዕድሉ፥ ርስቱም ነውና።
ፊንሐስ
23የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም በክብር ሦስተኛ ነው፤
ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶአልና፥
ሕዝቡንም ለማስተማር አስነሥቶታልና፥
በልቡናው ቸርነትም ከእግዚአብሔር ፈቃድ የተነሣ ለእስራኤል አስተሰረየ።
24ስለዚህም ለሕዝቡ የቅዱሳንን ሥርዐት ያስተምራቸው ዘንድ፥
ለእርሱና ለዘሩም ለዘለዓለም ደገኛ ክህነት ይሆን ዘንድ የሰላም ኪዳንን አጸናለት።
25ከነገደ ይሁዳ ለተወለደ ለዳዊት ልጅም ጌጥ ይሆን ዘንድ፥
በሕጉ ጸንቶ የሚኖር የልጁ መንግሥትም እድል ይሆን ዘንድ፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የመንግሥት ርስት ለዘሩ ብቻ ይሆን ዘንድ ከይሁዳ ወገን ለሆነው ለዕሴይ ልጅ ለዳዊት እንዳደረገው ቃል ኪዳን እንዲሁ የአሮን ርስት ለዘሩ ይሆን ዘንድ” ይላል።
26በልቡናቸውም ጥበብን ያሳድርባቸው ዘንድ፥
በዘመናቸው ሁሉ ክብራቸውና በረከታቸው እንዳይጠፋባቸው፥
ወገኖቹንም በእውነት ይገዟቸው ዘንድ ከልጆቹ ጋራ ለእርሱ ክህነት ርስቱ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 45: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ