መጽሐፈ ሲራክ 46
46
ኢያሱና ካሌብ
1የነዌ ልጅ ኢያሱም በሰልፍ ውስጥ ጽኑዕ ነው። ከሙሴም ቀጥሎ ትንቢት ተናገረ፤
እንደ ስሙም ታላቅ ሆነ፤
እግዚአብሔር የመረጣቸውንም ከመከራ አዳናቸው፤
ለእስራኤል ምድራቸውን ያወርሳቸው ዘንድ ጠላቶቻቸውን ተበቅሎ አጠፋ።
2እጁን በአነሣ ጊዜ፥
በከተሞቻቸውም ላይ ጦሩን በወረወረ ጊዜ ከበረ።
3ከእርሱ አስቀድሞ እንደ እርሱ የሆነ ማንነው?
እርሱ እግዚአብሔርም ጠላቶቹን ተዋጋለት።
4ፀሐይ በቃሉ የቆመች አይደለምን?
አንዲቱስ ቀን ሁለት ቀን የሆነች አይደለምን?
5በዙሪያው ያሉ ጠላቶቹ በአስጨነቁት ጊዜ
ኀያልና ልዑል እግዚአብሔርን ጠራው፤
ገናና እግዚአብሔርም በበረድና በጽኑዕ ኀይል መለሰለት።
6በተጣሏቸው በአሕዛብም ላይ አዘነበባቸው፤
የተዋጓቸውንም በገደል ውስጥ አጠፏቸው፤
ሕዝቡ ኀይሉን ያውቁ ዘንድ የሚዋጋላቸው እግዚአብሔር ነውና፤
ኀይሉን አከታትሎ ከእነርሱ ጋር አደረገላቸው።
7በሙሴም ዘመን ከእነርሱ ጋር ይቅርታን አደረገ፤
እርሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በጠላት ፊት ተከራከሩ፤
ሕዝቡንም በደልን ከለከሏቸው፥
ክፉ እንጕርጕሮንም አስተዉአቸው።
8ከስድስት መቶ ሺህ አርበኞችም የዳኑ እነርሱ ሁለቱ ብቻ ናቸው፤
ወተትና ማር ወደምታፈስስ ወደ ከነዓንም ገቡ።
9እግዚአብሔርም ለካሌብ ኀይልን ሰጠው፤
እስኪያረጅም ድረስ ከእርሱ ጋራ ኖረ፤
ወደ ከፍተኛውም ምድር አወጣው።
ልጆቹም ርስታቸውን ተካፈሉ።
10የእስራኤል ልጆች ሁሉ እግዚአብሔርን መከተል መልካም እንደ ሆነ ያውቁ ዘንድ።
መሳፍንት
11በየስማቸው የተጠሩ የእስራኤል መሳፍንት፥
ልቡናቸውም ያልሰሰነ ሰዎች ሁሉ፥
እግዚአብሔርንም ያልተዉት ሰዎች ሁሉ፥
ስም አጠራራቸው የተባረከ ይሁን።
12በኖሩበትም ሀገር አጥንቶቻቸውን ደስ ይበላቸው፤
ልጆቻቸውም ይባረኩ፥ ይክበሩ።#ግሪኩ “የተባረከ ስማቸውም በልጆቻቸው ይኑር” ይላል።
13ሳሙኤልም በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነበር፤
በእግዚአብሔርም ዘንድ ነቢይ ነበር፤
ለሕዝቡ ንጉሥን ቀብቶ አነገሠ።
14በእግዚአብሔርም ሕግ ማኅበሩን ገዛ፤
እግዚአብሔርም ያዕቆብን አከበረው።
15በእምነቱም ትንቢት ጸና፤
በቃሉም እውነተኛ ራእይ ተገለጠ።
16የበግም ጠቦት ሲሠዋ ጠላቶቹ ከብበው በአስጨነቁት ጊዜ
ኀያል እግዚአብሔርን ጠራው።
17እግዚአብሔርም በሰማይ አንጐደጐደ፤
በታላቅ ጩኸትም ድምፁን አሰማ።
18የፍልስጥኤምንና የጤሮስንም ነገሥታት ሁሉ አጠፋቸው።
19የሚሞትበትም ቀን ሳይደርስ ለእግዚአብሔርና ለመሢሑ፥
የማንንም ሰው ገንዘብ ከገንዘባቸው እስከ ጫማ ድረስ እንዳልወሰደ፥
ከእነርሱም የከሰሰው እንደሌለ አዳኘ።
20ከሞተም በኋላ ትንቢት ተናገረ፤
የንጉሡንም ሞት ተናገረ፤
ከምድርም ተነሥቶ ቃሉን በትንቢት ከፍ አደረገ።
የሕዝቡንም በደል አጠፋ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 46: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ