መጽሐፈ ሲራክ 47
47
ናታንና ዳዊት
1ከእርሱም በኋላ ናታን ተነሣ፤
በዳዊትም ዘመን ትንቢት ተናገረ።
2ስቡን ከድኅነቱ መሥዋዕት እንደሚለዩ
እንደዚሁ ዳዊት ከእስራኤል ልጆች ተለየ።
3በእርሱም ዘንድ አንበሳ እንደ ፍየል ጠቦት፥
ግስላም እንደ በግ ጠቦት ነበር።
4በወጣትነቱ አርበኛን የገደለ አይደለምን?
እጁንስ አንሥቶ ድንጋይ በወነጨፈ ጊዜ ጎልያድን ግንባሩን የመታው፥ ናላውንም የበጠበጠው አይደለምን?
የሕዝቡንስ ተግዳሮት ያስወገደ አይደለምን?
5ልዑል እግዚአብሔርን ለምኖታልና
በሰልፍ ኀይለኛውን ሰው ይገድል ዘንድ
የወገኖቹንም ቀንድ ያጸና ዘንድ በቀኝ እጁ ኀይልን ሰጠው።
6ዘፋኞቹም ዳዊትን ዐሥር ሺህ ገዳይ አሉት፤
በእግዚአብሔርም በረከት አመሰገኑት፤
የክብር ዘውድንም ተቀዳጀ።
7በዙሪያው ያሉ ጠላቶቹንም ቀጠቀጣቸው፤
ጠላቶቹ ፍልስጥኤማውያንንም አዋረዳቸው፤
እስከ ዛሬም ድረስ ቀንዳቸውን#“ኀይላቸውን ደመሰሰ” ማለት ነው። ሰበረ።
8በሚሠራው ሥራ ሁሉ ቅዱስና ልዑል እግዚአብሔርን በምስጋና ቃል አመሰገነ፤
በፍጹም ልቡም ፈጣሪውን አመሰገነው፤ ወደደውም።
9በመሠዊያውም ፊት መዘምራንን መደበ፤
የቃላቸውም ዜማ ያማረና የጣፈጠ ነበር።
10መልካም በዓልንም አደረገ፤
ዓመቱን ሁሉ ደስ አሰኘ፥
ቅዱስ ስሙንም አመሰገነው፤
ቅድስናውም ከነግህ ጀምሮ ይነገራል።#ምዕ. 47 ቍ. 10 በግሪክ ሰባ. ሊ. “ዜማውም በቤተ መቅደሱ ከነግህ ጀምሮ ያስተጋባ ነበር” ይላል።
11እግዚአብሔርም ኀጢአቱን አስተሰረየለት፤
ቀንዱንም ለዘለዓለሙ ከፍ ከፍ አደረገለት፤
የተባረከች መንግሥትን፥ የእስራኤልንም የክብር ዙፋን ሰጠው።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የንጉሥነትን ቃል ኪዳን ሰጠው” ይላል።
ስለ ንጉሥ ሰሎሞን
12ከእርሱም በኋላ ጠቢብ የሆነ ልጁ ተተካለት
ስለ እርሱም በስፋት ኖረ።
13ሰሎሞንም በሰላም ዘመን ነገሠ፥
እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ሁሉ አሳረፈው፤
በስሙ ቤትን ሠራ፤ የዘለዓለም መቅደሱንም አዘጋጀ።
14ሰሎሞን ሆይ፥ ከሕፃንነትህ ጀምሮ ጥበብህ እንዴት በዛ፤
ማስተዋልህም እንደ ፈሳሽ ውኃ ሞላ።
15ጥበብህ ምድርን ሸፈነቻት፥
ምሳሌህን፥ የነገርህንም ትርጓሜ አበዛህ።
16ስምህም እስከ ሩቅ ደሴት ድረስ ተሰማ፤
ስለ ሰላምህም ተወደድህ።
17ሀገሮችም ስለ መዝሙርህ፥ ስለ ምሳሌህ፥
ስለ እንቆቅልሾችህና ስለ ትርጓሜዎችህ አደነቁህ።
18የእስራኤል አምላክ በተባለ በእግዚአብሔር ስም፥
ወርቁንም እንደ እርሳስ አደለብኸው፤ ብርንም እንደ ማዕድን ቅልቅል መላኸው።
19ሴቶች ልቡናህን ለወጡት፤
በሥጋህም ሠለጠኑብህ።
20ክብርህን አስነቀፍህ፤ ዘርህንም አሳደፍኽ፤
በልጆችህም ላይ መቅሠፍትንና ጥፋትን አመጣህ፤
ስንፍናህም አስደነገጠኝ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በስንፍናህም አዘኑ” ይላል።
21መንግሥትህም ተከፈለ፤
ዐመፀኛ መንግሥትም ከኤፍሬም ወጣች።
22እግዚአብሔር ግን ቸርነቱን አልተወም፤
ሥራውንም አላጠፋም፤ የጻድቃኑንም ልጆች አልደመሰሰም፤
የሚወዱትንም ሰዎች ዘር አላጠፋም፤
ለያዕቆብም ቅሬትን ሰጠው፥ ከእርሱም ለዳዊት ሥርን ሰጠው።
ሮብአምና ኢዮርብአም
23ሰሎሞንም እንደ አባቶቹ አረፈ
ከእርሱም በኋላ አእምሮ የሌለው ልጁን ለእስራኤል ተወ።
ይኸውም ሕዝቡን በምክሩ ያሳመፃቸው ሮብዓም ነው።
እስራኤልን ያሳታቸው፥ ለኤፍሬምም የኀጢአት መንገድን ያሳየ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ነበረ።
24ኀጢአታቸውም ፈጽሞ በዛ፥
ከሀገራቸውም አስወጥቶ ሰደዳቸው።
25ፍዳቸውም እስክትደርስባቸው ድረስ ኀጢአትን ሁሉ ፈለጓት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 47: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ