መጽሐፈ ሲራክ 49
49
ንጉሡ ኢዮስያስ
1የኢዮስያስ መታሰቢያው በቀማሚ ብልሃት እንደ ተቀመመ ሽቱ ነው፤
እንደ ማርም በአፍ ሁሉ ጣፋጭ ነው፤
በመጠጥ ግብዣም ጊዜ እንደ ዘፈን ነው።
2እርሱ የቀና ነው፤
ሕዝቡንም መለሳቸው፤
የኀጢአትንም ርኵሰት ሁሉ አስወገደ።
3ልቡናውንም ወደ እግዚአብሔር አቀና፤
በኃጥኣንም ዘመን ጽድቅን አጸናት።
4ከዳዊት፥ ከሕዝቅያስና ከኢዮስያስ በቀር ሁሉም በድለዋል፤
የልዑልን ሕግ ትተዋልና፤ የይሁዳም ነገሥታት አለቁ።
5ኀይላቸውን ለሌላ ሰጥተዋልና፥
ክብራቸውንም ለሌላ ሕዝብ ሰጥተዋልና።
ነቢዩ ኤርምያስ
6የተመረጠችውንና የተቀደሰችውን ከተማ አቃጠሏት።
መከራ አጽንተውባታልና እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ትንቢት ጎዳናዋን አጠፉ።
7አሠቃይተውታልና፤ እርሱ ግን ነቢይ ይሆን ዘንድ፥
ይነቅል ዘንድ፥ ያጠፋም ዘንድ፥
እንደዚሁም ይተክል ዘንድ፥ ይሠራም ዘንድ በእናቱ ማኅፀን ተመረጠ።
ነቢዩ ሕዝቅኤል
8ሕዝቅኤልም የጌትነቱን ራእይ አየ፥
እግዚአብሔርንም በኪሩቤል ሠረገላ ላይ አየው።
9ጠላቶቹንም በመዓት ዐሰባቸው፥
የጻድቃንንም ጎዳናቸውን በመልካም አቀና።
10የዐሥራ ሁለቱ ነቢያትም አጽሞቻቸው በየቦታቸው ለመለሙ፤
ያዕቆብን አጽናንተውታልና፥ በታመነ ተስፋም አድነውታልና።
11ዘሩባቤልን እንዴት እናገንነው ይሆን!
እርሱስ በቀኝ እጅ እንዳለ እንደ ሐቲም ቀለበት ነው።
12የዮሴዴቅ ልጅ ዮሴዕም እንዲሁ ነበረ፤
በዘመናቸውም ቤተ መቅደስን ሠሩ፤
ለዘለዓለም ክብር የተዘጋጀ የእግዚአብሔርንም ሕዝብ አከበሩት።
13የነሕምያም መታሰቢያው ብዙ ነው፤
የወደቀችውን ቅጽር አነሣልን፤
ደጃፎችንም አቆመልን፤
ቍልፍንም ሠራልን፥ ቤታችንንም ገነባልን።
14እንደ ሄኖክ ያለ ሰው በምድር የተፈጠረ የለም፤
እርሱ ከዚህ ዓለም ተወሰደ።
15እንደ ዮሴፍም ያለ ሰው አልተወለደም፤
ለወንድሞቹ አለቃ ሆነ፤
ለሕዝቡም ኀይል ሆነ፥ ለአጽሞቹም ይቅርታን አገኘ።#ግሪኩ “አጥንቶቹም ክብርን አገኙ” ይላል።
16ሴምና ሴት ከሰው ይልቅ ከበሩ፥
አዳምም ከተፈጠረው ሕያው ፍጥረት ሁሉ ከበረ፤
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 49: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ