መጽሐፈ ጥበብ 7
7
ሰው ሁሉ መዋቲ ስለ መሆኑ
1እኔም እንደ ሁሉ እኩል መዋቲ ሰው ነኝ፤ አስቀድሞ የተፈጠረ የምድራዊ አዳም ልጅም ነኝ፥ በእናቴ ማኅፀንም ሥጋ ሆኜ ተቀርጫለሁ። 2በመገናኘት ጊዜ ከአባት ዘርና ከመኝታ ፈቃድ ተገኝቼ፥ ዐሥር ወር በደምነት ረግቼ ኖርሁ። 3በተፈጠርሁም ጊዜ እንደ ሰው ሁሉ ነፍስን ነሣሁ፥ በመከራዬም ምሳሌ ወደ ምድር ወረድሁ፤ የቃልም መጀመርያ እንደ ሁሉ ልቅሶን አለቀስሁ። 4በጨርቅ ተጠቅልዬ በጥንቃቄ አደግሁ። 5ከነገሥታት ወገን የልደቱ መጀመሪያ ልዩ የሆነ የለምና። 6የሁሉም ወደዚህ ዓለም አመጣጡ አንዲት ናት፥ የሁሉም መውጣቱ እኩል ነው።
ሰሎሞን ለጥበብ የነበረው ፍቅር
7ስለዚህ ነገር ጸለይሁ፤ ዕውቀትም ተሰጠኝ፤ ለመንሁ፤ የጥበብም መንፈስ ወደ እኔ መጣ። 8ከበትረ መንግሥትና ከዙፋንም ይልቅ አከበርኋት፤ ብዕልንም ከእርስዋ ጋር ሳመዛዝን እንደ ኢምንት አደረግኋት። 9ወርቅ ሁሉ በእርሷ ዘንድ እንደ ጥቂት አሸዋ ነውና፤ ብሩም በእርስዋ ዘንድ እንደ ጭቃ ነውና፥ ዋጋ በሌለው ዕንቍ አልመሰልኋትም። 10ከሕይወትና ከውበትም ፈጽሜ ወደድኋት፤ ከእርሷ የሚወጣ የብርሃን ነጸብራቅ አይወሰንምና፥ ደግሞም አይጠፋምና ስለ ብርሃን ፋንታ ትሆነኝ ዘንድ መረጥኋት።
11ከእርሷ ጋር በአንድነት በጎ ነገር ሁሉ መጣልኝ፤ ቍጥር የሌለው ባለጠግነትም በእጆችዋ አለ። 12ጥበብ የእነዚህ ሁሉ አበጋዛቸው ናትና በሁሉ ደስ አለኝ፤ ጥበብ የእነዚህ ሁሉ አስገኛቸው እንደ ሆነች አላወቅሁም ነበር። 13ይህን ባወቅሁ ጊዜ ያለ ክፋትና ያለ ቅንአት እርሷን እሰጣለሁ፤ ብልጽግናዋንም አልሰውርም። 14ለሰውም የማያልቅ መዝገብ ናት፤ ገንዘብ ያደረጓትም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ደረሱ፤ ሀብትን የምትገልጽ የምክር ሥራ ስለ ሆነችም ተወዳጇት።
15ለእኔም እግዚአብሔር የሚወደደውን ነገር እናገር ዘንድ፥ ለሚሰጠውም ሰው የሚገባውን አስብ ዘንድ ጥበብን ሰጠኝ። ወደ ጥበብ የሚመራ፥ ጠቢባንንም ቅን የሚያደርግ እርሱ ነውና። 16እኛ ሁላችን በእጁ ነንና፤ ነገራችንም ሁሉ ሥራችንንም ማወቅና መረዳት በእጁ ነውና። 17ያለ ሐሰት ነዋሪ የሚሆን የዕውቀት ነገርን ሰጠኝ፤ ዓለም ጸንቶ የሚኖርበትንም ሥርዐት፥ የፀሐይን፥ የጨረቃንና የከዋክብትንም ሥራ አውቅ ዘንድ፤ 18የዘመኑን መጀመሪያውንና መጨረሻውን፥ መካከሉንም፥ የቀኑን መመላለስ፥ የጊዜውንም መለዋወጥ፥ 19የዘመናትን ዑደት፥ የከዋክብትንም አኗኗር፥ 20የእንስሳንም ጠባይ፥ የአራዊትንም ቍጣ፥ የነፋሳትንም ኀይል፥ የሰውንም አሳብ፥ ዛፎችንም ለይቶ ማወቅ፥ የሥሮችንም ተግባር ኀይል አውቅ ዘንድ ሰጠኝ። 21የሥራው ሁሉ አስገኝ እርሱ ጥበብን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሥራው ሁሉ አስገኝ የሆነች ጥበብ አስተምራኛለች” ይላል። አስተምሮኛልና የተገለጸውንና የተሰወረውን ሁሉ ዐወቅሁ።
የጥበብ ጠባይ
22በእርስዋ የማስተዋል መንፈስ አለና፤ እርሱም ቅዱስ፥ በልደት ብቸኛ የሆነ፥ አንድ ሲሆን ሀብቱ ብዙ የሆነ፥ ረቂቅ፥ እንቅስቃሴውም የፈጠነ፥ ቃሉ የሚያምር፥ ጠቢብ፥ ዕድፈትም የሌለበት፥ የማይደክም፥ ጥንት የሌለው፥ ነዋሪ፥ ቸርነትን የሚወድ፥ ፈጣን፥ በጎ ነገርን ለማድረግ የሚከለክለው የሌለ፥ 23ሰው ወዳጅ፥ የጥበብ ወዳጅዋ፥ ዐዋቂ፥ እውነተኛ፥ ግዳጅ የሌለበት፥ ትዕግሥተኛ፥ ሁሉን የሚችል፥ ሁሉንም የሚጐበኝ፥ ንጹሓትና አስተዋዮች፥ ረቂቃትም በሆኑ ነፍሳት የሚያድር ነው። 24የጥበብ እንቅስቃሴዋ ከእንቅስቃሴ ሁሉ ይፈጥናልና። በሁሉም ዘንድ በስፋት ትመላለሳለች፤ ስለ ንጽሕናዋም ጽርየት በሁሉ ትሄዳለች። 25የእግዚአብሔር የኀይሉ እስትንፋስ ናትና፥ አርአያው የታወቀ፥ ክቡርና ንጹሕ የሆነ የኀያል አምላክ የክብሩ መገለጫ ናት። ስለዚህ የሚያገኛት ምንም ርኵሰት የለም። 26የቀዳማዊ ብርሃን ነጸብራቅ ናትና፥ የማትጨልም የእግዚአብሔር የሥራው መስታዋትም ናትና፥ የቸርነቱም አርኣያ ናትና። 27አንዲት ስትሆን ሁሉን ማድረግ ትችላለች፤ ራስዋም እየኖረች ሁሉን ታድሳለች፥ በየትውልዱም በጻድቃን ሰውነት ትተላለፋለች፤ የእግዚአብሔርም ወዳጆችና ነቢያቱ ታደርጋቸዋለች።
28እግዚአብሔር ከጥበብ ጋር ከሚኖር ሰው በቀር የሚወድደው የለምና። 29እርስዋ ከፀሐይ ይልቅ በመልክ ታምራለችና፥ ከከዋክብትም ሥርዐት ሁሉ ትበልጣለች፤ ከብርሃን ጋርም በምትመዘንበት ጊዜ በልጣ በፊቱ ትገኛለች። 30ብርሃኑን ሌሊት ይለውጠዋልና፥ ጥበብን ግን ምንም ክፉ ነገር አይበረታታባትም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 7: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ