መጽሐፈ ጥበብ 6
6
የገዥዎች ሐላፊነት
1ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤ አስተውሉም፤ የምድር ዳርቻንም የምትገዙ መኳንንት ሆይ፥ ዕወቁ። 2ብዙ ምድርን የምትገዙ፥ በሠራዊትም ብዛት የምትታበዩ ስሙ። 3እግዚአብሔር ኀይልን ሰጥትዋችኋልና፤ ግዛታችሁም ከልዑል ዘንድ ነው፤ ምግባራችሁንም የሚመረምር እርሱ ነው፤ ምክራችሁንም ይመረምራል። 4እናንተ የመንግሥቱ መልእክተኞች ስትሆኑ የቀና ፍርድን እንዴት አትፈርዱም? ሕጉንስ እንዴት አልጠበቃችሁም? በእግዚአብሔርስ መንገድ እንዴት አልሄዳችሁም? 5ፈጥኖ የሚቃወማችሁ ድንጋፄን በላያችሁ ያመጣል፥ ቍርጥ ፍርድ በመኳንንት ላይ ይሆናልና። 6ለተዋረደው ድሃ ግን ከቸርነት ሥራ የተነሣ ይቀልለታል፤ ኀይለኞች ሰዎች ግን በጽኑዕ ምርመራ ይመረመራሉ። 7እግዚአብሔር ፊት አይቶ አያዳላምና፤ የታላቁንም መከበር አያፍርምና፤ እንደዚሁም ታናሹንና ታላቁን ስለ ፈጠረ ለገዡና ለተገዡ ሁሉ ያስባል፤ ይወስንላቸዋልም። 8በኀያላን ግን ጽኑዕ ምርመራ ይደርስባቸዋል። 9ክፉዎችና ግፈኞች#“ክፉዎችና ግፈኞች” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። መኳንንት ሆይ፥ ጥበብን እንድታውቁና እንዳትሰነካከሉ ነገሬ ለእናንተ ነው። 10እውነተኛ ትእዛዙን ዐውቀው የሚጠብቁ በእውነት ይከብራሉና የተማሯትም ሰዎች ምሕረትን ያገኛሉና። 11እንግዲህ ወዲህ ነገሬን ተመኝዋት፥ ውደዷትም፤ ይቅርታንና ቸርነትንም ታገኙ ዘንድ ተመከሩ።
የጥበብ ዋጋ
12ጥበብ ፈጽማ የጐላች ናት፤ ውበቷም አይጠወልግም፤ የሚወድዷትም ሰዎች ፈጥነው ያዩአታል፥ የሚፈልጉአትም ያገኙአታል። 13ለሚወዷትም ትደርስላቸዋለች፤ አስቀድማም ትገለጥላቸዋለች። 14በደጃፉ ስትጠብቀው ሁል ጊዜ እርሱ ያገኛታልና ወደርስዋ የሚገሠግሥ ሰው አይደክምም። 15እርስዋን ማሰብ የዕውቀት ፍጻሜ ነውና፥ ፈጥኖ ስለ እርስዋ የሚተጋ ሰው ያለ ኀዘን ይኖራል። 16ለእርስዋ የሚገቧትን ሰዎች ፈልጋ ትመጣለችና፥ በመንገድም ድንገት እንደ ሥዕል አምራ ትታያቸዋለች፤ በአሳብም ሁሉ ትገናኛቸዋለች። 17የጥበብ መጀመሪያ ተግሣጽን መውደድ ነው፤ ተግሣጽንም ማሰብ እርሷን መውደድ ነው። 18እርሷንም መውደድ ሕጓን መጠበቅ ነው፤ ሕጓንም መስማት ሕይወትን መረዳት ነው። 19ሕይወትም ሰውን ወደ እግዚአብሔር የቀረበ ታደርጋለች። 20ጥበብን መውደድ ወደ መንግሥት ታደርሳለችና።
21የአሕዛብ ነገሥታት ሆይ፥ ዙፋንንና በትረ መንግሥትን ከወደዳችሁ ለዘለዓለም ትነግሡ ዘንድ ጥበብን አክብሯት። 22ጥበብ ምንድን ናት? እንደ ምንስ ነበረች? እኔ እነግራችኋለሁ፤ የተሰወረ ምሥጢሯንም ከእናንተ አልሰውርም። ነገር ግን ከጥንት ጀምሮ አኳኋኗን እመረምራለሁ፤ እርሷን ማወቅንም የተገለጠ አደርጋለሁ፤ እውነትንም አልተላለፍም። 23በምቀኛ ቅንአት አልኖርም፤ እንዲህ ያለ ሰው ከጥበብ ጋራ አንድ አይሆንምና። 24የጠቢባን ብዛት የዓለም መድኀኒት ነውና። 25አስተዋይ ንጉሥም ለሕዝቡ ጠበቃ ነው፤ በቃሌም ተመከሩ፤ ትጠቀማላችሁም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 6: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ