ትንቢተ ዘካርያስ 14
14
1እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፥ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ። 2አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ ለሰልፍ እሰበስባለሁ፣ ከተማይቱም ትያዛለች፥ ቤቶችም ይበዘበዛሉ፥ ሴቶችም ይነወራሉ፣ የከተማይቱም እኵሌታ ለምርኮ ይወጣል፥ የቀረው ሕዝብ ግን ከከተማ አይጠፋም። 3እግዚአብሔርም ይወጣል፥ በሰልፍም ቀን እንደ ተዋጋ ከእነዚያ አሕዛብ ጋር ይዋጋል። 4በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ፣ ደብረ ዘይትም በመካከል ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል፣ የተራራውም እኵሌታ ወደ ሰሜን፥ እኵሌታውም ወደ ደቡብ ይርቃል። 5የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ይደርሳልና በተራሮች ሸለቆ ትሸሻላችሁ፣ በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን ከሆነው ከምድር መናወጥ ፊት እንደ ሸሻችሁ ትሸሻላችሁ፣ አምላኬ እግዚአብሔርም ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል። 6በዚያም ቀን በረዶና ውርጭ እንጂ ብርሃን አይሆንም። 7አንድ ቀንም ይሆናል፥ እርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ይሆናል፣ ቀንም አይሆንም፥ ሌሊትም አይሆንም፣ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል። 8በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፣ እኵሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኵሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይሄዳል፣ ይህ በበጋና በክረምት ይሆናል።
9እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፣ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፥ ስሙም አንድ ይሆናል። 10ምድር ሁሉ ከጌባ ጀምሮ በኢየሩሳሌምም ደቡብ በኩል እስካለችው እስከ ሬሞን ድረስ ተለውጣ እንደ ዓረባ ትሆናለች፣ እርስዋም ከፍ ከፍ ትላለች፥ ከብንያምም በር ጀምሮ እስከ ፊተኛው በር ስፍራ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ፥ ከሐናንኤልም ግንብ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መጥመቂያ ድረስ በስፍራዋ ትኖራለች። 11ሰዎችም ይኖሩባታል፥ ከዚያም ወዲያ እርግማን አይሆንም፣ ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትኖራለች።
12እግዚአብሔርም ከኢየሩሳሌም ጋር የተዋጉትን አሕዛብ ሁሉ የሚቀሥፍበት ቸነፈር ይህ ነው፣ በእግራቸው ሲቆሙ ሥጋቸው ይበሰብሳል፥ ዓይኖቻቸውም በዓይነስባቸው ውስጥ ይበሰብሳሉ፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። 13በዚያም ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ሽብር በእነርሱ ላይ ይሆናል፣ እያንዳንዱም የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፥ እጁም በባልንጀራው እጅ ላይ ይነሣል። 14ይሁዳም ደግሞ በኢየሩሳሌም ውስጥ ሆኖ ይዋጋል፣ በዙሪያም ያሉት የአሕዛብ ሁሉ ሀብት እጅግ ብዙ ወርቅና ብር ልብስም ይሰበሰባል። 15በፈረስና በበቅሎ፥ በግመልና በአህያ፥ በዚያም ሰፈር ባለ እንስሳ ሁሉ ላይ የሆነ ቸነፈር እንደዚያ ያለ ቸነፈር ይሆናል።
16በኢየሩሳሌም ላይ ከመጡት ከአሕዛብ ሁሉ የቀሩት ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ፥ የዳስ በዓልንም ያከብሩ ዘንድ በየዓመቱ ይወጣሉ። 17ከምድርም ወገኖች ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለማይወጡ ለእነርሱ ዝናብ አይዘንብላቸውም። 18የግብጽም ወገን ባይወጣ ወደዚያም ባይመጣ፥ እግዚአብሔር የዳስ በዓልን ያከብሩ ዘንድ የማይወጡትን አሕዛብ የሚቀሥፍበት ቸነፈር በእርሱ ላይ ይሆናል። 19የግብጽ ቅጣት፥ የዳስ በዓልንም ያከብሩ ዘንድ የማይወጡት የአሕዛብ ሁሉ ቅጣት እንደዚህ ይሆናል። 20በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኵራ ላይ፦ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ተብሎ ይጻፋል፣ በእግዚአብሔርም ቤት ያሉ ምንቸቶች በመሠዊያው ፊት እንዳሉ ዳካዎች ይሆናሉ። 21በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶችም ሁሉ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ ይሆናሉ፣ የሚሠውትም ሰዎች ሁሉ ይመጣሉ ከእነዚያም ወስደው ይቀቅሉባቸዋል፣ በዚያም ቀን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቤት ከነዓናዊው ከእንግዲህ ወዲያ አይገኝም።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 14: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ