የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 11

11
1እንዲህም ሆነ፥ ከአንድ ወር በኋላ አሞናዊው ናዖስ ወጣ፥ በኢያቢስ ገለዓድም ሰፈረ፥ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ፦ ቃል ኪዳን አድርግልን፥ እኛም እንገዛልሃለን አሉት። 2አሞናዊውም ናዖስ፦ ቀኝ ዓይናችሁን ሁሉ በማውጣት ቃል ኪዳን አደርግላችኋለሁ፥ በእስራኤልም ሁሉ ላይ ስድብ አደረጋለሁ አላቸው። 3የኢያቢስም ሽማግሌዎች፦ ወደ እስራኤል አገር ሁሉ መልክተኞችን እንድንልክ ሰባት ቀን ቆይልን፥ ከዚያም በኋላ የሚያድነን ባይኖር ወደ አንተ እንመጣለን አሉት። 4መልክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ነገር በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ፥ ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። 5እነሆም፥ ሳኦል በሬዎቹን ተከትሎ ከእርሻው መጣ፥ ሳኦልም፦ ሕዝቡ የሚያለቅስ ምን ሆኖ ነው? አለ። የኢያቢስንም ሰዎች ነገር ነገሩት።
6ይህንም ነገር በሰማው ጊዜ በሳኦል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደ፥ ቁጣውም እጅግ ነደደ። 7ጥምዱንም በሬዎች ወስዶ ቆራረጣቸው፥ ወደ እስራኤልም ዳርቻ ሁሉ በመልክተኞቹ እጅ ሰደደና፦ ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ የማይወጣ ሁሉ፥ በበሬዎቹ እንዲሁ ይደረግ አለ። ድንጋጤም በሕዝቡ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደቀ፥ እንደ አንድ ሰውም ሆነው ወጡ። 8በቤዜቅም ቆጠራቸው፥ የእስራኤልም ልጆች ሦስት መቶ ሺህ፥ የይሁዳም ሰዎች ሠላሳ ሺህ ነበሩ። 9የመጡትንም መልክተኞች፦ የኢያቢስ ገለዓድን ሰዎች፦ ነገ ፀሐይ በተኮሰ ጊዜ ማዳን ይሆንላችኋል በሉአቸው አሉአቸው። መልክተኞችም መጥተው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሩ፥ ደስም አላቸው። 10የአያቢስም ሰዎች፦ ነገ እንወጣላችኋለን፥ ደስ የሚያሰኛችሁንም አድርጉብን አሉ። 11በነጋውም ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ወገን አደረጋቸው፥ ወገግም ባለ ጊዜ ወደ ሰፈሩ መካከል ገቡ፥ ቀትርም እስኪሆን ድረስ አሞናውያንን መቱ፥ የቀሩትም ተበተኑ፥ ሁለትም በአንድ ላይ ሆነው አልቀሩላቸውም።
12ሕዝቡም ሳሙኤልን፦ ሳኦል አይንገሥብን ያሉ እነማናቸው? አውጡአቸውና እንግደላቸው አሉት። 13ሳኦልም፦ ዛሬ እግዚአብሔር ለእስራኤል ማዳን አድርጎአልና ዛሬ አንድ ሰው አይሞትም አለ። 14ሳሙኤልም ሕዝቡን፦ ኑ፥ ወደ ጌልገላ እንሂድ፥ በዚያም መንግሥቱን እናድስ አላቸው። 15ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄዱ፥ በዚያም ሳኦልን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ አነገሡት፥ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ፥ በዚያም ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ አደረጉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ