አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 24
24
1እንዲህም ሆነ፥ ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ፦ እነሆ፥ ዳዊት በዓይንጋዲ ምድረ በዳ አለ የሚል ወሬ ደረሰለት። 2ሳኦልም ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎች ወሰደ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ለመፈለግ የበረሀ ፍየሎች ወደ ነበሩባቸው ዓለቶች ሄደ። 3በመንገድም አጠገብ ወዳሉት የበጎች ማደሪያዎች መጣ፥ በዚያም ዋሻ ነበረ፥ ሳኦልም ወገቡን ይሞክር ዘንድ ከዚያ ገባ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር። 4የዳዊትም ሰዎች፦ እነሆ፥ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ በዓይንህም ደስ የሚያሰኝህን ታደርግበታለህ ብሎ እግዚአብሔር የነገርህ ቀን፥ እነሆ፥ ዛሬ ነው አሉት። ዳዊትም ተነሥቶ የሳኦልን መጎናጸፊያ ዘርፍ በቀስታ ቆረጠ። 5ከዚያም በኋላ እንዲህ ሆነ፥ የሳኦልን የልብሱን ዘርፍ ስለቆረጠ የዳዊት ልብ በኅዘን ተመታ። 6ሰዎቹንም፦ እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው አላቸው። 7ዳዊትም በዚህ ቃል ሰዎቹን ከለከላቸው፥ በሳኦልም ላይ ይነሡ ዘንድ አልተዋቸውም፥ ሳኦልም ከዋሻው ተነሥቶ መንገዱን ሄደ።
8ከእርሱም በኋላ ዳዊት ደግሞ ተነሣ፥ ከዋሻውም ወጣ፥ ከሳኦልም በኋላ፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ብሎ ጮኸ፥ ሳኦልም ወደ ኋላው ተመለከተ፥ ዳዊትም ወደ ምድር ተጎንብሶ እጅ ነሣ። 9ዳዊትም ሳኦልን አለው፦ እነሆ፥ ዳዊት ክፉ ነገር ይሻብሃል የሚሉህን ሰዎች ቃል ለምን ትሰማለህ? 10እነሆ፥ ዛሬ በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ እንደ ሰጠህ ዓይንህ አይታለች፥ አንተንም እንድገድልህ ሰዎች ተንገሩኝ፥ እኔ ግን፦ በእግዚአብሔር የተቀባ ነውና እጄን በጌታዬ ላይ አልዘረጋም ብዬ ራራሁልህ። 11ደግሞም፥ አባቴ ሆይ፥ የልብስህ ዘርፍ በእጄ እንዳለ ተመልክተህ እወቅ፥ የልብስህንም ዘርፍ በቆረጥሁ ጊዜ አልገደልሁህም፥ ስለዚህም በእጄ ክፋትና በደል እንደሌለ፥ አንተም ነፍሴን ልትወስድ ምንም ብታሳድደኝ እንዳልበደልሁህ ተመልክተህ እወቅ። 12እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፥ እግዚአብሔርም አንተን ይበቀልልኝ፥ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም። 13በጥንት ምሳሌ፦ ከኃጢአተኞች ኃጢአት ይወጣል እንደ ተባለ፥ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም። 14የእስራኤል ንጉሥ ማንም ለማሳደድ መጥቶአል? አንተስ ማንን ታሳድዳለህ? የሞተ ውሻን ወይስ ቁንጫን ታሳድዳለህን? 15እንግዲህ እግዚአብሔር ዳኛ ይሁን፥ በእኔና በአንተም መካከል ይፍረድ፥ አይቶም ይምዋገትልኝ፥ ከእጅህም ያድነኝ።
16እንዲህም ሆነ፥ ዳዊት ይህን ቃል ለሳኦል መናገር በፈጸመ ጊዜ፥ ሳኦል፥ ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለ፥ ሳኦልም ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 17ዳዊትን አለው፦ እኔ ክፉ በመለስሁልህ ፋንታ በጎ መልሰህልኛልና አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ። 18እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ አልገደልኸኝምና ለእኔ መልካም እንዳደረግህልኝ አንተ ዛሬ አሳየኸኝ። 19ጠላቱን አግኝቶ በመልካም መንገድ ሸኝቶ የሚሰድድ ማን ነው? ስለዚህ ለእኔ ስላደረግኸው ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ። 20አሁንም፥ እነሆ፥ አንተ በእርግጥ ንጉሥ እንድትሆን የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ እንድትጸና እኔ አውቃለሁ። 21አሁን እንግዲህ ከእኔ በኋላ ዘሬን እንዳትቆርጥ ከአባቴም ቤት ስሜን እንዳታጠፋው በእግዚአብሔር ማልልኝ። 22ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፥ ሳኦልም ወደ ቤቱ ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ አምባው ወጡ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 24: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ