አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 28
28
1እንዲህም ሆነ፥ በዚያ ወራት ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ዘንድ ፍልስጥኤማውያን ጭፍሮቻቸውን ለሰልፍ ሰበሰቡ፥ አንኩስም ዳዊትን፦ አንተና ሰዎችህ ከእኔ ጋር ወደ ሰልፍ እንድትወጡ በእርግጥ እወቅ አለው። 2ዳዊትም አንኩስን፦ አሁን ባሪያህ የሚያደርገውን ታያለህ አለው። አንኩስም ዳዊትን፦ እንግዲህ በዘመኑ ሁሉ ራሴን ጠባቂ አደርግሃለሁ አለው።
3ሳሙኤል ግን ሞቶ ነበር፥ እስራኤልም ሁሉ አልቅሰውለት ነበር፥ በከተማውም በአርማቴም ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር አጥፍቶ ነበር። 4ፍልስጥኤማውያንም ተሰብስበው መጡ በሱነምም ሰፈሩ፥ ሳኦልም እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ በጊልቦዓም ሰፈሩ። 5ሳኦልም የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ባየ ጊዜ ፈራ፥ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ። 6ሳኦልም እግዚአብሔርን ጠየቀ፥ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም። 7ሳኦልም ባሪያዎቹን፦ ወደ እርስዋ ሄጄ እጠይቅ ዘንድ መናፍስትን የምትጠራ ሴት ፈልጉልኝ አላቸው፥ ባሪያዎቹም፦ እነሆ፥ መናፍስትን የምትጠራ አንዲት ሴት በዓይንዶር አለች አሉት።
8ሳኦልም መልኩን ለውጦ ሌላ ልብስም ለብሶ ሄደ፥ ሁለትም ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ በሌሊትም ወደ ሴቲቱ መጡ። እርሱም፦ እባክሽ፥ በመናፍስት አምዋርቺልኝ፥ የምልሽንም አስነሽልኝ አላት። 9ሴቲቱም፦ እነሆ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር እንዳጠፋ ሳኦል ያደረገውን ታውቃለህ፥ ስለ ምን እኔን ለማስገደል ወጥመድ ለነፍሴ ታደርጋለህ? አለችው። 10ሳኦልም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም ብሎ በእግዚአብሔር ማለላት። 11ሴቲቱም፦ ማንን ላስነሣልህ? አለች፥ እርሱም፦ ሳሙኤልን አስነሽልኝ አለ። 12ሴቲቱም ሳሙኤልን ባየች ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኸች፥ ሴቲቱም ሳኦልን፦ አንተ ሳኦል ስትሆን ለምን አታለልኸኝ? ብላ ተናገረችው። 13ንጉሡም፦ አትፍሪ፥ ያየሽው ምንድር ነው? አላት። ሴቲቱም ሳኦልን፦ አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ አለችው። 14እርሱም፦ መልኩ ምን ዓይነት ነው? አላት። እርስዋም፦ ሽማግሌ ሰው ወጣ፥ መጎናጸፊያም ተጎናጽፎአል አለች። ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ሆነ አወቀ፥ በፊቱም ተጎነበሰ፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣ።
15ሳሙኤልም ሳኦልን፦ ለምን አወክኽኝ? ለምንስ አስነሣኸኝ? አለው። ሳኦልም መልሶ፦ ፍልስጥኤማውያን ይወጉኛልና እጅግ ተጨንቄአለሁ፥ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቆአል፥ በነቢያት ወይም በሕልም አልመለሰልኝም፥ ስለዚህም የማደርገውን ታስታውቀኝ ዘንድ ጠራሁህ አለው። 16ሳሙኤልም አለ፦ እግዚአብሔር ከራቀህ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ? 17እግዚአብሔርም በቃሌ እንደ ተናገረ አድርጎአል፥ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል። 18የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና፥ በአማሌቅም ላይ ታላቅ የሆነ ቁጣውን አላደረግህምና ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ነገር አድርጎብሃል። 19እግዚአብሔርም እስራኤልን ከአንተ ጋር በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል፥ ነገም አንተና ልጆችህ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ፥ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ጭፍራ ደግሞ በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል።
20ሳኦልም በዚያን ጊዜ በቁመቱ ሙሉ በምድር ላይ ወደቀ፥ ከሳሙኤልም ቃል የተነሣ እጅግ ፈራ። በዚያም ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ እንጀራ አልበላምና ኃይል አልቀረለትም። 21ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጣች፥ እጅግም ደንግጦ እንደ ነበረ አይታ፦ እነሆ፥ እኔ ባሪያህ ቃልህን ሰማሁ፥ ነፍሴንም በእጄ ጣልሁ፥ የነገርኽኝንም ቃል ሰማሁ። 22አሁን እንግዲህ አንተ ደግሞ የባሪያህን ቃል እንድትሰማ እለምንሃለሁ፥ በፊትህም ቁራሽ እንጀራ ላኑርልህ በመንገድም ስትሄድ ትበረታ ዘንድ ብላ አለችው። 23እርሱ ግን፦ አልበላም ብሎ እንቢ አለ፥ ነገር ግን ባሪያዎቹና ሴቲቱ አስገደዱት፥ ቃላቸውንም ሰማ ከምድርም ተነሥቶ በአልጋ ላይ ተቀመጠ። 24ለሴቲቱም ማለፊያ እንቦሳ ነበራት፥ ፈጥና አረደችው፥ ዱቄቱንም ወስዳ ለወሰችው፥ ቂጣም እንጀራ አድርጋ ጋገረችው። 25በሳኦልና በባሪያዎቹም ፊት አቀረበችው፥ በልተውም ተነሡ፥ በዚያም ሌሊት ሄዱ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 28: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ