የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 29

29
1ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን ሁሉ ወደ አፌቅ ሰበሰቡ፥ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ባለው ውኃ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። 2የፍልስጥኤማውያንም አለቆች በመቶ በመቶ በሺህ በሺህ እየሆኑ ያልፉ ነበር፥ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ ጋር በኋለኛው ጭፍራ በኩል ያልፉ ነበር። 3የፍልስጥኤማውያንም አለቆች፦ እነዚህ ዕብራውያን በዚህ ምን ያደርጋሉ? አሉ፥ አንኩስም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች፦ ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል ባሪያ ዳዊት አይደለምን? እርሱም በእነዚህ ቀኖች በእነዚህ ዓመታት ከእኔ ጋር ነበረ፥ ወደ እኔም ከተጠጋበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ምንም አላገኘሁበትም አላቸው። 4የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን ተቆጥተው፦ ይህ ሰው ባስቀመጥኸው ስፍራ ይቀመጥ ዘንድ ይመለስ፥ በሰልፍ ውስጥ ጠላት እንዳይሆነን ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይውረድ፥ ከጌታው ጋር በምን ይታረቃል? የእነዚህን ሰዎች ራስ በመቁረጥ አይደለምን? 5ወይስ ሴቶች፦ ሳኦል ሺህ ገደለ፥ ዳዊት እልፍ ገደል ብለው በዘፈን የዘመሩለት ይህ ዳዊት አይደለምን? አሉት።
6አንኩስም ዳዊትን ጠርቶ፦ ሕያው እግዚአብሔርን! አንተ ቅን ነህ፥ ከእኔም ጋር በጭፍራው በኩል መውጣትህና መግባትህ በፊቴ መልካም ነው፥ ወደ እኔም ከመጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አንዳች ክፋት አላገኘሁብህም፥ ነገር ግን በአለቆች ዘንድ አልተወደድህም። 7አሁንም ተመልሰህ በደኅና ሂድ፥ በፍልስጥኤማውያንም አለቆች ዓይን ክፋት አታድርግ አለው። 8ዳዊትም አንኩስን፦ ምን አድርጌአለሁ? ሄጄስ ከጌታዬ ከንጉሡ ጠላቶች ጋር እንዳልዋጋ፥ በፊትህ ከተቀመጥሁ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በእኔ በባሪያህ ምን አግኝተህብኛል? አለው። 9አንኩስም መልሶ ዳዊትን፦ እንደ አምላክ መልእክተኛ በዓይኔ ፊት መልካም እንደ ሆንህ አውቃለሁ፥ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያን አለቆች፦ ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይወጣም አሉ። 10አሁንም አንተ ከአንተም ጋር የመጡ የጌታህ ባሪያዎች ማልዳችሁ ተነሡ፥ ሲነጋም ተነሥታችሁ ሂዱ አለው። 11ዳዊትና ሰዎቹም ማልደው ይሄዱ ዘንድ፥ ወደ ፍልስጥኤማውያንም አገር ይመለሱ ዘንድ ተነሡ። ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ