ትንቢተ ሕዝቅኤል 26
26
1እንዲህም ሆነ፥ በአሥራ አንደኛው ዓመት ከወሩ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ጢሮስ በኢየሩሳሌም ላይ፦ እሰይ፥ የአሕዛብ በር የነበረች ተሰብራለች ወደ እኔም ተመልሳለች፥ እርስዋ ፈርሳለችና እኔ እሞላለሁ ብላለችና 3ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ባሕርም ሞገድዋን እንደምታወጣ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን አወጣብሻለሁ። 4የጢሮስንም ቅጥሮች ያጠፋሉ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፥ ትቢያዋንም ከእርስዋ እፍቃለሁ፥ የተራቈተ ድንጋይ አደርጋታለሁ። 5በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ትሆናለች፥ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ለአሕዛብም ብዝበዛ ትሆናለች። 6በሜዳ ያሉትም ሴቶች ልጆችዋ በሰይፍ ይገደላሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ ከሰሜን የነገሥታት ንጉሥ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነዖርን ከፈረሶችና ከሰረገሎች ከፈረሰኞችም ከጉባኤና ከብዙ ሕዝብ ጋር በጢሮስ ላይ አመጣለሁ። 8በሜዳ ያሉትን ሴቶችን ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፥ አምባም ይሠራብሻል አፈርንም ይደለድልብሻል ጋሻም ያነሣብሻል። 9ማፍረሻውን በቅጥርሽ ላይ ያደርጋል፥ ግንቦችሽንም በምሳር ያፈርሳል። 10ከፈረሶቹም ብዛት የተነሣ ትቢያቸው ይከድንሻል፥ ሰዎችም በተናደች ቅጥር ወደ ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ ሲገባ፥ ከፈረሰኞችና ከመንኵራኵሮች ከሰረገሎችም ድምፅ የተነሣ ቅጥርሽ ትናወጣለች። 11በፈረሶቹ ኮቴ ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረመርማል፥ ሕዝብሽንም በሰይፍ ይገድላል፥ የብርታትሽም ሐውልት ወደ ምድር ይወድቃል። 12ብልጥግናሽንም ይማርካሉ፥ ሸቀጥሽንም ይበዘብዛሉ፥ ቅጥርሽንም ያፈርሳሉ፥ ተድላ የምታደርጊባቸውን ቤቶችሽን ያጠፋሉ፥ ድንጋይሽንና እንጨትሽን መሬትሽንም በባሕር ውስጥ ይጥላሉ። 13የዘፋኞችሽንም ብዛት ዝም አሰኛለሁ፥ የመሰንቆሽም ድምፅ ከዚያ ወዲያ አይሰማም። 14የተራቈተ ድንጋይ አደርግሻለሁ የመረብም ማስጫ ትሆኛለሽ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አትሠሪም፥ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
15ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላታል፦ የተወጉት ባንቋረሩ ጊዜ፥ በውስጥሽ እልቂት በሆነ ጊዜ፥ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች ይነዋወጡ የለምን? 16የባሕርም አለቆች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፥ መጐናጸፊያቸውን ያወጣሉ ወርቀዘቦ ልብሳቸውንም ያወልቃሉ፥ መንቀጥቀጥን ለብሰው በመሬት ላይ ይቀመጣሉ፥ ሁልጊዜም ይንቀጠቀጣሉ በአንቺም ይደነቃሉ። 17በአንቺም ላይ ሙሾ ያሞሻሉ፥ እንዲህም ይሉሻል፦ በባሕር የተቀመጥሽ በባሕርም ውስጥ የጸናሽ፥ ከሚቀመጡብሽም ጋር በዙሪያሽ የሚኖሩትን ሁሉ ያስፈራሽ፥ የከበርሽ ከተማ ሆይ፥ እንዴት ጠፋሽ! 18አሁን በውድቀትሽ ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፥ በባሕርም ውስጥ ያሉ ደሴቶች ከመጥፋትሽ የተነሣ ይደነግጣሉ።
19ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰው እንደሌለባቸው ከተሞች ባድማ ከተማ ባደረግሁሽ ጊዜ፥ ቀላዩንም ባወጣሁብሽ ጊዜ ብዙ ውኆችም በከደኑሽ ጊዜ፥ 20የቀድሞ ሕዝብ ወዳሉበት ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋር አወርድሻለሁ፥ የሚኖርብሽም እንዳይገኝ ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ቀድሞ በፈረሰችው ስፍራ፥ በታችኛይቱ ምድር አኖርሻለሁ፥ ጌጥሽንም በሕያዋን ምድር አላኖርም። 21ለድንጋጤ አደርግሻለሁ እንግዲህም አትኖሪም፥ ትፈለጊአለሽ ለዘላለምም አትገኚም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 26: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ