ትንቢተ ሕዝቅኤል 27
27
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጢሮስ ሙሾ አድርግ፥ 3በባሕር መግቢያ የምትኖር በብዙም ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ጋር ንግድን የምታደርግ ጢሮስንም እንዲህ በላት፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ፥ አንቺ፦ በውበት ፍጹም ነኝ ብለሻል። 4ዳርቻሽ በባሕር ውስጥ ነው፥ ሠሪዎችሽ ውበትሽን ፈጽመዋል። 5ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሳኔር ጥድ ሠርተዋል፥ ደቀልንም ይሠሩልሽ ዘንድ ከሊባኖስ ዝግባ ወስደዋል። 6ከባሳን ኮምቦል መቅዘፊያሽን ሠርተዋል፥ በዝሆን ጥርስ ከታሻበ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍ መቀመጫዎችሽን ሠርተዋል። 7ዓላማ እንዲሆንልሽ ሸራሽ ከግብጽ በፍታና ከወርቅ ዘቦ ተሠርቶአል፥ መደረቢያሽም ከኤሊሳ ደሴቶች ሰማያዊና ቀይ ሐር ተሠርቶአል። 8የሲዶናና የአራድ ሰዎች ቀዛፎችሽ ነበሩ፥ ጢሮስ ሆይ፥ ጥበበኞችሽ በአንቺ ዘንድ ነበሩ የመርከቦችሽም መሪዎች ነበሩ። 9በአንቺ ውስጥ የነበሩ የጌባል ሽማግሌዎችና ጥበበኞችዋ ስብራትሽን ይጠግኑ ነበር፥ ከአንቺም ጋር ይነግዱ ዘንድ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞቻቸው በመካከልሽ ነበሩ። 10ፋርስና ሉድ ፉጥም በሠራዊትሽ ሰልፈኞችሽ ነበሩ፥ ጋሻና ራስ ቍርም በአንቺ ውስጥ ያንጠለጥሉ ነበር፥ እነርሱም ውበትሽን ሰጡ። 11የአራድ ሰዎችና ሠራዊቶችሽ በቅጥሮችሽ ላይ በዙሪያ ነበሩ፥ ገማዳውያንም በግንቦችሽ ውስጥ ነበሩ፥ ጋሻቸውንም በዙሪያ በቅጥርሽ ላይ አንጠለጠሉ፥ ውበትሽንም ፈጽመዋል።
12ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ተርሴስ ነጋዴሽ ነበረች፥ በብርና በብረት በቈርቈሮና በእርሳስ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 13ያዋንና ቶቤል ሞሳሕም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፥ የሰዎችን ነፍሳትና የናሱን ዕቃ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 14ከቴርጋማ ቤትም የነበሩት ሰዎች በፈረሶችና በፈረሰኞች በበቅሎዎችም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 15የድዳን ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ፥ ይለውጡ ዘንድ የዝሆን ጥርስና ዞጲ አመጡልሽ። 16ከሥራሽ ብዛት የተነሣ ሶርያ ነጋዴሽ ነበረች በበሉርና በቀይ ሐር በወርቀ ዘቦም በጥሩ በፍታም በዛጐልም በቀይ ዕንቁም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 17ይሁዳና የእስራኤል ምድር ነጋዴዎችሽ ነበሩ፥ የሚኒትን ስንዴ ጣፋጭም እንጕቻ፥ ማር ዘይትም በለሳንም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 18ከሥራሽ ብዛትና ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ደማስቆ ነጋዴሽ ነበረች፥ በኬልቦን የወይን ጠጅ በነጭም በግ ጠጕር ይነግዱ ነበር። 19ዌንዳንና ያዋን ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር፥ ከኦሴል የተሠራ ብረትና ብርጕድ ቀረፋም ሸቀጥሽ ነበረ። 20ድዳን በከብት ላይ ለመቀመጥ በመረሻት ነጋዴሽ ነበረች። 21ዓረብና የቄዳር አለቆች ሁሉ የእጅሽ ነጋዴዎች ነበሩ፥ በጠቦቶችና በአውራ በጎች በፍየሎችም በእነዚህ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር። 22የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች እነዚህ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፥ በጥሩ ሽቶና በክብር ድንጋይ ሁሉ በወርቅም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 23ካራንና ካኔ ዔድንም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፥ አሦርና ኪልማድ ነጋዴዎችሽ ነበሩ። 24እነዚህ ባማረ ልብስ በሰማያዊ ካባ በወርቀ ዘቦም፥ በዝግባ በተሠራች በገመድም በታሰረች በግምጃም በተሞላች ሳጥን በገበያሽ ይነግዱ ነበር። 25የተርሴስ መርከቦች ሸቀጥሽን የሚሸከሙ ነበሩ፥ አንቺም ተሞልተሽ ነበር በባሕርም ውስጥ እጅግ ከበርሽ።
26ቀዛፊዎችሽ ወደ ትልቁ ወኃ አመጡሽ፥ የምሥራቅ ነፋስ በባሕር ውስጥ ሰበረሽ። 27ብልጥግናሽና ሸቀጥሽ ንግድሽም መርከበኞችሽም መርከብ መሪዎችሽም ሰባራሽንም የሚጠግኑ ነጋዴዎችሽም በአንቺም ዘንድ ያሉ ሰልፈኞችሽ ሁሉ በውስጥሽ ካሉት ጉባኤ ሁሉ ጋር በወደቅሽበት ቀን በባሕር ውስጥ ይወድቃሉ። 28ከመርከብ መሪዎች ጩኸት ድምፅ የተነሣ በዙሪያሽ ያሉ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ። 29ቀዛፊዎችም ሁሉ መርከበኞችም መርከብ መሪዎችም ሁሉ ከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ በመሬትም ላይ ይቆማሉ፥ 30ድምፃቸውንም በአንቺ ላይ ያሰማሉ፥ ምርር ብለውም ይጮኻሉ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ይነሰንሳሉ፥ በአመድም ውስጥ ይንከባበላሉ፥ 31ስለ አንቺም የራሳቸውን ጠጕር ይላጫሉ ማቅም ያሸርጣሉ በነፍስ ምሬትም ስለ አንቺ መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ። 32በትካዜያቸውም ልቅሶ ያነሡልሻል፥ ስለ አንቺም ሙሾ ያሞሻሉ እንዲህም ይላሉ፦ በባሕር መካከል ጠፍቶ እንደ ቀረ እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነው? 33ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ ብዙ አሕዛብን አጥግበሻል፥ በብልጥግናሽና በንግድሽ ብዛት የምድርን ነገሥታት ባለ ጠጎች አድርገሻል። 34አሁን ግን በጥልቅ ውኃ ውስጥ በባህር ተሰብረሻል ንግድሽና ጉባኤሽ ሁሉ በመካከልሽ ወድቀዋል። 35በደሴቶች የሚኖሩ ሁሉ ተደንቀውብሻል፥ ነገሥታቶቻቸውም እጅግ ፈርተዋል ፊታቸውም ተለውጦአል። 36የአሕዛብ ነጋዴዎች አፍዋጩብሽ፥ አንቺ ለድንጋጤ ሆነሻል፥ እስከ ዘላለምም አትገኚም።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 27: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ