ትንቢተ ሕዝቅኤል 32
32
1እንዲህም ሆነ፥ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በለው፦ የአሕዛብን አንበሳ መስለህ ነበር፥ ነገርግን እንደ ባሕር ዘንዶ ሆነሃል፥ በወንዞችህም ወጥተሃል፥ ወኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል። 3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በብዙ አሕዛብ ጉባኤ መረቤን እዘረጋብሃለሁ፥ እነርሱም በመረቤ ያወጡሃል። 4በምድርም ላይ እተውሃለሁ፥ በምድረ በዳም ፊት እጥልሃለሁ፥ የሰማይንም ወፎች ሁሉ አሳርፍብሃለሁ፥ የምድርንም አራዊት ሁሉ ከአንተ አጠግባቸዋለሁ። 5ሥጋህን በተራሮች ላይ አደርጋለሁ ሸለቆቹንም በሬሳህ ክምር እሞላለሁ። 6የምትዋኝባትንም ምድር እስከ ተራሮች ድረስ በደምህ አጠጣለሁ፥ መስኖችም ከአንተ ይሞላሉ። 7ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፥ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም። 8የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በላይህ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9በማታውቃቸውም አገሮች ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ጥፋትህን ባመጣሁ ጊዜ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ። 10ብዙም አሕዛብን አስደንቅብሃለሁ ሰይፌንም በፊታቸው ባወዛወዝሁ ጊዜ ነገሥታቶቻቸው ስለ አንተ እጅግ አድርገው ይፈራሉ፥ በወደቅህበትም ቀን እያንዳንዱ ስለ ነፍሱ በየጊዜው ሁሉ ይንቀጠቀጣል።
11ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል። 12በኃያላን ሰይፍ የሕዝብህን ብዛት እጥላለሁ፥ ሁሉ የአሕዛብ ጨካኞች ናቸው፥ የግበጽንም ትዕቢት ያጠፋሉ ብዛትዋም ሁሉ ይጠፋል። 13በብዙም ውኃ አጠገብ ያሉትን እንስሶች ሁሉ አጠፋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲያ የሰው እግር አያደፈርሰውም የእንስሳም ኮቴ አይረግጠውም። 14በዚያን ጊዜ ውኃቸውን አጠራለሁ፥ ወንዞቻቸውም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15የግብጽንም ምድር ባድማና ውድማ ባደረግሁ ጊዜ፥ ሞላዋንም ያጣች ምድር ባደረግኋት ጊዜ፥ የሚኖሩባትንም ሁሉ በቀሠፍሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 16የሚያለቅሱበት ልቅሶ ይህ ነው፥ የአሕዛብ ቈነጃጅት ያለቅሱበታል፥ ስለ ግብጽና ስለ ብዛትዋ ሁሉ ያለቅሱበታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17እንዲህም ሆነ፥ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ብዛት ዋይ በል፥ እርስዋንና የብርቱዎችን አሕዛብ ሴቶች ልጆች ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ታችኛው ምድር ጣላቸው። 19በውበት የምትበልጪው ማን ነው? ውረጂ ካልተገረዙትም ጋር ተኚ። 20በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፥ ለሰይፍ ተሰጥታለች፥ እርስዋንና ብዛትዋን ሁሉ ጐትቱ። 21የኃያላን አለቆች በሲኦል ውስጥ ሆነው ከረዳቶቹ ጋር ይናገሩታል፥ በሰይፍም የተገደሉት ያልተገረዙ ወርደው ተኝተዋል።
22አሦርና ጉባኤዋ ሁሉ በዚያ አሉ፥ መቃብራቸው በዙሪያቸው ነው፥ ሁሉም በሰይፍ ወድቀው ተገደሉ። 23መቃብራቸው በጕድጓዱ በውስጠኛው ክፍል ነው፥ ጉባኤዋም በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፥ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል።
24ኤላምም በዚያ አለች ብዛትዋም ሁሉ በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፥ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል ሳይገረዙም ወደ ታችኛው ምድር ወርደዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። 25በተገደሉት መካከል ከብዛትዋ ሁሉ ጋር መኝታን አድርገውላታል፥ መቃብርዋ በዙሪያዋ ነው ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፥ በሕያዋንም ምድር ያስፈሩ ነበር ወደ ጉድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል፥ በተገደሉትም መካከል ተሰጥተዋል።
26ሞሳሕና ቶቤል ብዛታቸውም ሁሉ በዚያ አሉ መቃብራቸውም በዙሪያቸው ነው፥ ሁሉም ሳይገረዙ በሰይፍ ተገድለዋል፥ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ነበርና። 27በሕያዋንም ምድር ኃያላኑን ያስፈሩ ነበርና መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ሲኦል ከወረዱ፥ ሰይፋቸውንም ከራሳቸው በታች ካደረጉ፥ ኃጢአታቸውም በአጥንታቸው ላይ ከሆነ ጋር ከወደቁ ካልተገረዙ ኃያላን ጋር ይተኛሉ። 28አንተም ባልተገረዙት መካከል ትሰበራለህ፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ትተኛለህ።
29ኤዶምያስና ነገሥታቶችዋ አለቆችዋም ሁሉ በዚያ አሉ፥ በሰይፍ ከተገደሉት ጋር በኃይላቸው ተኝተዋል፥ ካልተገረዙትና ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ይተኛሉ። 30የሰሜን አለቆች ሁሉ ሲዶናውያንም ሁሉ ከተገደሉት ጋር ወርደው በዚያ አሉ፥ በኃይላቸውም ያስፈሩ በነበረው ፍርሃት አፍረዋል፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ሳይገረዙ ተኝተዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱት ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል።
31በሰይፍ የተገደሉ ፈርዖንና ሠራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል ፈርዖንም ስለ ብዛቱ ሁሉ ይጽናናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 32መፈራቱን በሕያዋን ምድር አድርጌአለሁ፥ ፈርዖንና ብዛቱም ሁሉ በሰይፍ በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ይተኛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 32: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ