የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 33

33
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብ ልጆች ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ከመካከላቸው ሰውን ወስደው ለራሳቸው ጕበኛ ቢያደርጉ፥ 3እርሱም በምድር ላይ የመጣውን ሰይፍ ባየ ጊዜ መለከትን ቢነፋ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፥ 4የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል። 5የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፥ ቢጠነቀቅስ ኖሮ ነፍሱን ባዳነ ነበር። 6ጕበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ ቢያይ መለከቱንም ባይነፋ ሕዝቡንም ባያስጠነቅቅ ሰይፍም መጥቶ አንድ ሰው ከእነርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኃጢአቱ ተወስዶአል ደሙን ግን ከጕበኛው እጅ እፈልጋለሁ።
7አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፥ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። 8ኃጢአተኛውን፦ ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ታስጠነቅቅ ዘንድ ባትናገር ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 9ነገር ግን ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።
10አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት፦ እናንተ፦ በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ እኛም ሰልስለንባቸዋል፥ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው። 11እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው። 12አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው፦ በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፥ ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፥ ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም። 13እኔ ጻድቁን፦ በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአትም ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም። 14እኔም ኃጢአተኛውን፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥ 15ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ የነጠቀውንም ቢመልስ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 16የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፥ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17ነገር ግን የሕዝብህ ልጆች፦ የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ይላሉ፥ ነገር ግን የእነርሱ መንገድ የቀና አይደለም። 18ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአትን ቢሠራ ይሞትባታል። 19ኃጢአተኛውም ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ በሕይወት ይኖርበታል። 20እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።
21እንዲህም ሆነ፥ በተማረክን በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፦ ከተማይቱ ተመታች አለኝ። 22ያመለጠውም ሳይመጣ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ በነጋውም ወደ እኔ እስኪመጣ ድረስ አፌን ከፈተ፥ አፌም ተከፈተች ከዚያም በኋላ እኔ ዲዳ አልሆንሁም።
23የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 24የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር ባሉ በባድማ ስፍራዎች የተቀመጡ፦ አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ፥ እኛም ብዙዎች ነን ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች ይላሉ። 25ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከደም ጋር ትበላላችሁ፥ ዓይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፥ ደምንም ታፈስሳላችሁ፥ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? 26ሰይፋችሁን ይዛችሁ ቆማችኋል፥ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፥ የባልንጀሮቻችሁንም ሚስቶች ታስነውራላችሁ፥ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? 27እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና በባድማ ስፍራዎች ያሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ በምድረ በዳ ያለውን ለአራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ፥ በአምባዎችና በዋሾች ያሉ በቸነፈር ይሞታሉ። 28ምድሪቱንም ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ የኃይልዋም ትዕቢት ይቀራል፥ የእስራኤልም ተራሮች ባድማ ይሆናሉ፥ ማንም አያልፍባቸውም። 29ስላደረጉትም ርኩሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ ባደርግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
30አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህ ልጆች በቅጥር አጠገብና በቤት ደጆች ውስጥ ስለ አንተ ይናገራሉ፥ እርስ በርሳቸውም፥ አንዱ ከአንዱ ጋር፦ እንሂድና እግዚአብሔር ያለው ቃል ምን እንደ ሆነ እንስማ ብለው ይናገራሉ። 31ሕዝብ እንደሚመጣ ወደ አንተ ይመጣሉ፥ እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ፥ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም፥ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፥ ልባቸው ግን ስስታቸውን ትከተላለች። 32እነሆ፥ አንተ መልካም ድምፅ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ በገና እንደሚጫወት ሰው ሆነህላቸዋል፥ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም። 33እነሆ፥ ይህ ይመጣል፥ በመጣም ጊዜ እነርሱ ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ