የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 34

34
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? 3ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፥ በጎቹን ግን አታሰማሩም። 4የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። 5እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። 6በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፥ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም።
7ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ 8ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔም ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ 9የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ 10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያስማሩም፥ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም።
11ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ። 12እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ፥ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። 13ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ ከአገሮችም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ አገራቸውም አመጣቸዋለሁ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በፈሳሾችም አጠገብ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ። 14በመልካም ማሰማርያ አሰማራቸዋለሁ ጕረኖአቸውም በረጅሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፥ በዚያ በመልካም ጕረኖ ውስጥ ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ። 15እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ፥ የወፈረውንና የበረታውንም አጠፋለሁ፥ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።
17ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ፥ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል፥ እፈርዳለሁ። 18የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? 19በጎቼም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ።
20ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ እነሆ፥ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ። 21እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥ 22ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፥ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ። 23በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፥ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፥ ያሰማራቸዋል እረኛም ይሆናቸዋል። 24እኔም እግዚአብሔር አምላክ እሆናቸዋለሁ ባሪያዬም ዳዊት በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፥ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።
25የሰላምን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ ክፉዎችንም አራዊት ከምድር አጠፋለሁ፥ ተዘልለውም በምድረ በዳ ይኖራሉ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ። 26እነርሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች ለበረከት አደርጋቸዋለሁ፥ ዝናቡንም በጊዜው አወርዳለሁ፥ የበረከት ዝናብ ይሆናል። 27የምድረ በዳም ዛፍ ፍሬውን ይሰጣል ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፥ በምድራቸውም ተዘልለው ይኖራሉ፥ የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 28እንግዲህም ለአሕዛብ ንጥቂያ አይሆኑም የምድርም አራዊት አይበሉአቸውም፥ ተዘልለውም ይቀመጣሉ የሚያስፈራቸውም የለም። 29የዝናን ተክል አቆምላቸዋለሁ እንግዲህም ከራብ የተነሣ በምድር አያልቁም፥ የአሕዛብንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አይሸከሙም። 30እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ፥ እነርሱም የእስራኤል ቤት ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 31እናንተም በጎቼ፥ የማሰማርያዬ በጎች፥ ሰዎች ናችሁ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ