የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 35

35
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርበት፥ እንዲህም በለው፦ 3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሴይር ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ እጄንም እዘረጋብሃለሁ ባድማና ውድማም አደርግሃለሁ። 4ከተሞችህንም አፈራርሳቸዋለሁ፥ አንተም ባድማ ትሆናለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ። 5የዘላለም ጥል ስላለህ በመከራቸውም ጊዜ በኋለኛይቱ የኃጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በሰይፍ እጅ ጥለሃቸዋልና 6ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ለደም አሳልፌ እሰጥሃለሁ ደምም ያሳድድሃል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ደምን ስላልጠላህ ደም ያሳድድሃል። 7የሴይርንም ተራራ ውድማ አደርገዋለሁ፥ የሚሄደውንና የሚመለሰውንም ከእርሱ አጠፋለሁ። 8ተራሮቹንም በተገደሉት ሰዎች እሞላለሁ፥ በኮረብቶችህና በሸለቆችህ በፈሳሾችህም ሁሉ ላይ በሰይፍ የተገደሉት ሁሉ ይወድቃሉ። 9ለዘላለምም ባድማ አደርግሃለሁ ከተሞችህም ሰው የማይኖርባቸው ይሆናሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
10እግዚአብሔርም በዚያ ሳለ፥ አንተ፦ እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች እነዚህም ሁለቱ አገሮች ለእኔ ይሆናሉ እኛም እንወርሳቸዋለን ብለሃልና 11ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና እንደ ቍጣህ መጠን እነርሱንም ጠልተህ እንዳደረግኸው እንደ ቅንዓትህ መጠን እኔ እሠራለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በፈረድሁብህም ጊዜ በእነርሱ ዘንድ የታወቅሁ እሆናለሁ። 12አንተም፦ ፈርሰዋል መብልም ሆነው ለእኛ ተሰጥተዋል ብለህ በእስራኤል ተራሮች ላይ የተናገርኸውን ስድብ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሰማሁት ታውቃለህ። 13በአፋችሁም ተመካችሁብኝ፥ ቃላችሁንም አበዛችሁብኝ፥ እኔም ሰምቼዋለሁ። 14ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ምድር ሁሉ ደስ ሲላት አንተን ባድማ አደርግሃለሁ። 15የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ ስለ ሆነ በላዩ ደስ እንዳለህ፥ እንዲሁ አደርግብሃለሁ፥ የሴይር ተራራ ሆይ፥ አንተና ኤዶምያስ ሁሉ ሁለንተናውም ባድማ ትሆናላችሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ