የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 36

36
1አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናግረህ፦ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በል። 2ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠላት በእናንተ ላይ፦ እሰይ፥ የጥንት ከፍታዎች ለእኛ ርስት ሆነዋል ብሎአልና 3ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለቀሩት አሕዛብ ርስት ትሆኑ ዘንድ በዙሪያችሁ ያሉ ባድማ አድርገዋችኋልና፥ ውጠዋችሁማልና፥ እናንተም የተናጋሪዎች ከንፈር መተረቻና የሕዝብ ማላገጫ ሆናችኋልና 4ስለዚህ፥ እናንተ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለፈሳሾችና ለሸለቆች ለምድረ በዳዎች ባዶ ለሆኑትም በዙሪያ ላሉት ለቀሩት አሕዛብ ምርኮና መሳቂያ ለሆኑት ከተሞች እንዲህ ይላል፥ 5ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያሳድዱአትና ይበዘብዙአት ዘንድ በልባቸው ሁሉ ደስታና በነፍሳቸው ንቀት ምድሬን ርስት አድርገው ለራሳቸው በሰጡ በቀሩት አሕዛብና በኤዶምያስ ሁሉ ላይ በቅንዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፥ 6ስለዚህ ስለ እስራኤል ምድር ትንቢት ተናገር፥ ለተራሮችና ለኮረብቶችም ለፈሳሾችና ለሸለቆችም እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የአሕዛብን ስድብ ስለ ተሸከማችሁ በቅንዓቴና በመዓቴ ተናግሬአለሁ፥ 7ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዙሪያችሁ ያሉ አሕዛብ ስድባቸውን በእርግጥ ይሸከማሉ ብዬ ምያለሁ።
8የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ እናንተ ግን ቅርንጫፎቻችሁን ታቈጠቍጣላችሁ፥ ይመጡም ዘንድ ቀርበዋልና ለሕዝቤ ለእስራኤል ፍሬአቸሁን ትሰጣላችሁ። 9እነሆ፥ እኔ ለእናንተ ነኝና፥ ወደ እናንተም እመለከታለሁ፥ እናንተም ትታረሳላችሁ ይዘራባችሁማል፥ 10እኔም የእስራኤልን ቤት ሰዎች ሁሉ ሁሉንም አበዛባችኋለሁ፥ በከተሞችም ሰዎች ይኖሩባቸዋል ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ፥ 11ሰውንና እንስሳውንም አበዛባችኋለሁ፥ እነርሱም ይበዛሉ ያፈሩማል፥ እንደ ጥንታችሁም ሰዎችን አኖርባችኋለሁ፥ ቀድሞም ካደረግሁላችሁ ይልቅ መልካም አደርግላችኋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 12ሰዎችንም፥ ሕዝቤን እስራኤልን፥ በእናንተ ላይ አስሄዳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይወርሱሻል ርስትም ትሆኛቸዋለሽ፥ ከእንግዲህም ወዲያ ልጅ አልባ አታደርጊአቸውም። 13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነርሱ፦ ሰው በሊታ ምድር ነሽ ሕዝብሽንም ልጅ አልባ የምታደርጊ ነሽ ብለዋችኋልና 14ስለዚህ ዳግመኛ ሰው በሊታ አትሆኝም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን ልጅ አልባ አታደርጊም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር 15ዳግመኛም የአሕዛብን ውርደት አላሰማብሽም፥ ዳግመኛም የአሕዛብን ስድብ አትሸከሚም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን አታሰናክዪም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 17የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት በምድራቸው በተቀመጡ ጊዜ በመንገዳቸውና በሥራቸው አረከሱአት፥ መንገዳቸውም በፊቴ እንደ መርገም አደፍ ነበረ። 18በምድር ላይ ስላፈሰሱት ደም በጣዖቶቻቸውም ስላረከሱአት መዓቴን አፈሰስሁባቸው፥ 19ወደ አሕዛብም በተንኋቸው ወደ አገሮችም ተዘሩ፥ እንደ መንገዳቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው። 20ወደ መጡባቸውም ወደ አሕዛብ በመጡ ጊዜ፥ ሰዎች እነርሱን፦ ከምድሩ የወጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እነዚህ ናቸው ሲሉአቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ። 21እኔ ግን የእስራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሱት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ራራሁላቸው።
22ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም። 23በአሕዛብም ዘንድ የረከሰውን፥ በመካከላቸው ያረከሳችሁትን ስሜን እቀድሰዋለሁ፥ በዓይናቸውም ዘንድ በተቀደስሁባችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 24ከአሕዛብም መካከል አወጣችኋለሁ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ። 25ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። 26አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፥ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። 27መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። 28ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፥ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። 29ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ፥ እህልንም እጠራዋለሁ አበዛውማለሁ ራብንም አላመጣባችሁም። 30ደግሞም የራብን ስድብ ከአሕዛብ ዘንድ እንዳትሸከሙ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ቡቃያ አበዛለሁ። 31ክፉውን መንገዳችሁንና መልካም ያይደለውን ሥራችሁንም ታስባላችሁ፥ ስለ በደላችሁና ስለ ርኵሰታችሁም ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። 32ይህን የሠራሁ ስለ እናንተ እንዳይደለ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ።
33ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ባነጻኋችሁበት ቀን በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ። 34ባድማ የነበረች በመንገደኛም ሁሉ ዓይን ዘንድ ባድማ የነበረች ምድር ትታረሳለች። 35ሰዎችም፦ ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆናለች፥ የፈረሱት ባድማ የሆኑት የጠፉትም ከተሞች ተመሽገዋል ሰውም የሚኖርባቸው ሆነዋል ይላሉ። 36በዙሪያችሁም የቀሩት አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር የፈረሱትን ስፍራዎች እንደ ሠራሁ ውድማ የሆነውንም እንደ ተከልሁ ያውቃሉ፥ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርገዋለሁ።
37ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለዚህ ደግሞ አደግላቸው ዘንድ የእስራኤል ቤት ይሹኛል ሰውንም እንደ መንጋ አበዛላቸዋለሁ። 38እንደ ተቀደሱ በጎች፥ በበዓላቶችዋ ቀን እንደሚሆኑ እንደ ኢየሩሳሌም በጎች፥ እንዲሁ የፈረሱት ከተሞች በሰዎች መንጋ ይሞላሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ