የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 44

44
1ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፥ ተዘግቶም ነበር። 2እግዚአብሔርም፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል። 3አለቃው ግን እርሱ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ይበላ ዘንድ ይቀመጥበታል፥ በበሩ ደጀ ሰላም መንገድ ይገባል በዚያም መንገድ ይወጣል።
4በሰሜኑም በር መንገድ በቤቱ ፊት አመጣኝ፥ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበር፥ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ። 5እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ልብ አድርግ ስለ እግዚአብሔርም ቤት ሥርዓትና ሕግ ሁሉ የምናገርህን ሁሉ በዓይንህ ተመልከት በጆሮህም ስማ፥ የቤቱንም መግቢያ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ። 6ለዓመፀኛው ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ 7እንጀራዬን፥ ስብንና ደምን፥ በምታቀርቡበት ጊዜ በመቅደሴ ውስጥ ይሆኑ ዘንድ ቤቴንም ያረክሱ ዘንድ በልባቸውና በሥጋቸው ያልተገረዙትን እንግዶችን ሰዎች አግብታችኋልና፥ እነርሱም በርኵሰታችሁ ሁሉ ላይ ይጨመሩ ዘንድ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና ርኵሰታችሁ ሁሉ ይብቃችሁ። 8በመቅደሴ ውስጥ ለራሳችሁ ሥርዓቴን ጠባቂዎች አደረጋችሁ እንጂ የተቀደሰውን ነገሬን ሥርዓት አልጠበቃችሁም።
9ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ልጆች መካከል ካሉት ሁሉ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ እንግዳ ሁሉ ወደ መቅደሴ አይግባ። 10ከእኔ ዘንድ የራቁ፥ እስራኤልም በሳቱ ጊዜ ጣዖታቸውን ተከትለው ከእኔ ዘንድ የሳቱ ሌዋውያን ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ። 11ነገር ግን በመቅደሴ ውስጥ አገልጋዮች ይሆናሉ፥ በቤቱም በሮች በረኞች ይሆናሉ በቤቱም ውስጥ ያገለግላሉ፥ ለሕዝቡም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን ያርዳሉ፥ ያገለግሉአቸውም ዘንድ በፊታቸው ይቆማሉ። 12በጣዖቶቻቸውም ፊት አገልግለዋቸው ነበሩና፥ ለእስራኤልም ቤት የኃጢአት ዕንቅፋት ሆነዋልና ስለዚህ እጄን በላያቸው አንሥቻለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይሸከማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 13ካህናትም ይሆኑኝ ዘንድ ወደ እኔ አይቀርቡም፥ ወደ ተቀደሰውም ነገሬና ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ነገር አይቀርቡም፥ እፍረታቸውንና የሠሩትንም ርኵሰታቸውን ይሸከማሉ። 14ነገር ግን ለአገልግሎቱ ሁሉና በእርሱ ውስጥ ለሚደረገው ሁሉ የቤቱን ሥርዓት ጠባቂዎች አደርጋቸዋለሁ።
15ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ከእኔ ዘንድ በሳቱ ጊዜ የመቅደሴን ሥርዓት የጠበቁ የሳዶቅ ልጆች ሌዋውያን ካህናት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ይቀርባሉ፥ ስቡንና ደሙንም ወደ እኔ ያቀርቡ ዘንድ በፊቴ ይቆማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16ወደ መቅደሴም ይገባሉ ያገለግሉኝም ዘንድ ወደ ገበታዬ ይቀርባሉ ሥርዓቴንም ይጠብቃሉ። 17ወደ ውስጠኛውም አደባባይ በር በገቡ ጊዜ የተልባ እግር ልብስ ይልበሱ፥ በውስጠኛውም አደባባይ በርና በቤቱ ውስጥ ባገለገሉ ጊዜ ከበግ ጠጕር አንዳች ነገር በላያቸው አይሁን። 18በራሳቸው ላይ የተልባ እግር መጠምጠሚያ ይሁን፥ በወገባቸውም ላይ የተልባ እግር ሱሪ ይሁን፥ የሚያወዛም ነገር አይታጠቁ። 19ወደ ውጭውም አደባባይ ወደ ሕዝብ በወጡ ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን ያውልቁ በተቀደሰውም ዕቃ ቤት ውስጥ ያኑሩት፥ ሕዝቡንም በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ሌላውን ልብስ ይልበሱ። 20ራሳቸውንም አይላጩ የራሳቸውንም ጠጕር ይከርከሙ እንጂ ጠጕራቸውን አያሳድጉ። 21ካህናቱም ሁሉ በውስጠኛው አደባባይ ሲገቡ የወይን ጠጅ አይጠጡ። 22መበሊቲቱንና የተፈታችይቱን አያግቡ፥ ከእስራኤል ቤት ዘር ግን ድንግሊቱን ወይም የካህን ሚስት የነበረችይቱን መበለት ያግቡ። 23በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ይለዩ ዘንድ ሕዝቤን ያስተምሩ፥ ንጹሕና ንጹሕ ባልሆነው መካከል ይለዩ ዘንድ ያሳዩአቸው። 24ክርክርም በሆነ ጊዜ ለመፍረድ ይቁሙ፥ እንደ ፍርዴ ይፍረዱ፥ በበዓላቴ ሁሉ ሕጌንና ሥርዓቴን ይጠብቁ፥ ሰንበታቴንም ይቀድሱ። 25እንዳይረክሱም ወደ ሞተ ሰው አይግቡ፥ ነገር ግን ለአባት ወይም ለእናት ወይም ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ ወይም ለወንድም ወይም ላልተዳረች እኅት ይርከሱ። 26ከነጻም በኋላ ሰባት ቀን ይቈጠርለት። 27በመቅደስም ውስጥ ያገለግል ዘንድ ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን፥ የኃጢአትን መሥዋዕት ያቅርብ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
28ርስት ይሆንላቸዋል፥ እኔ ርስታቸው ነኝ፥ በእስራኤልም ዘንድ ግዛት አትስጡአቸው፥ እኔ ግዛታቸው ነኝ። 29የእህሉን ቍርባንና የኃጢአትን መሥዋዕት የበደልንም መሥዋዕት ይበላሉ፥ በእስራኤልም ዘንድ እርም የሆነው ነገር ሁሉ ለእነርሱ ይሆናል። 30የበኵራቱ ሁሉ መጀመሪያ ከየዓይነቱ ከቍርባናችሁም ሁሉ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለካህናት ይሆናል፥ በቤታችሁም ውስጥ በረከት ያድር ዘንድ የዱቄታችሁን በኵራት ለካህናቱ ትሰጣላችሁ። 31የበከተውንና የተሰበረውን፥ ወፍ ወይም እንስሳ ቢሆን፥ ካህናት አይብሉት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ