ትንቢተ ሕዝቅኤል 45
45
1ርስትም አድርጋችሁ ምድርን በዕጣ በምታካፍሉበት ጊዜ ከምድር የተቀደሰውን የዕጣ ክፍል መባ አድርጋችሁ ወደ እግዚአብሔር ታቀርባላችሁ። ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል፥ በዳርቻው ሁሉ ዙሪያውን የተቀደሰ ይሆናል። 2ከእርሱም ርዝመቱ አምስት መቶ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ አራት ማዕዘን የሆነ ቦታ ለመቅደሱ ይሆናል፥ በዙሪያውም ባዶ ስፍራ የሚሆን አምሳ ክንድ ይሆናል። 3ከዚያው ልክ ደግሞ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም አሥር ሺህ ክንድ የሆነ ስፍራ ትለካለህ፥ በእርሱም ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን የሆነ መቅደስ ይሆናል። 4ከምድርም የተቀደሰ የዕጣ ክፍል ይሆናል፥ እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ለሚቀርቡ ለመቅደሱ አገልጋዮች ለካህናቱ ይሆናል፥ ለቤቶቻቸውም የሚሆን ስፍራ ለመቅደስም የሚሆን የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል። 5ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ዕፍራ ለቤቱ አገልጋዮች ለሌዋውያን ይሆናል፥ ለሚቀመጡባቸውም ከተሞች ለራሳቸውም የርስት ይዞታ ይሆናል። 6ለከተማይቱም ይዞታ በተቀደሰው የዕጣ ክፍል መባ አጠገብ ወርዱ አምስት ሺህ ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ የሆነውን ስፍራ ታደርጋላችሁ። እርሱም ለእስራኤል ቤት ሁሉ ይሆናል። 7ለአለቃውም የሆነ የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ አጠገብ በዚህና በዚያ ይሆናል፥ በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ ፊት በምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ በምሥራቅም በኩል ወደ ምሥራቅ ይሆናል፥ ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል። 8ይህም በእስራኤል ዘንድ ይዞታ ይሆንለታል፥ አለቆቼም ለእስራኤል ቤት ምድሪቱን እንደ ነገዳቸው መጠን ይሰጡአቸዋል እንጂ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም።
9ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል አለቆች ሆይ፥ ይብቃችሁ፥ ግፍንና ብዝበዛን አስወግዱ፥ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ፥ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አርቁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 10እውነተኛ ሚዛን እውነተኛም የኢፍ መስፈሪያ እውነተኛውም የባዶስ መስፈሪያ ይሁንላችሁ። 11የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ አንድ ይሁን፥ የባዶስ መስፈሪያ የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል፥ የኢፍ መስፈሪያውም የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ይሁን። መስፈሪያው እንደ ቆሮስ መስፈሪያ ይሁን። 12ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ይሁን፥ ሀያ ሰቅል፥ ሀያ አምስት ሰቅል፥ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ምናን ይሁንላችሁ።
13የምታቀርቡት መባ ይህ ነው፥ ከአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ ክፍል፥ ከአንድም ቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ ክፍል ትሰጣላችሁ። 14የዘይቱም ደንብ፥ ከእያንዳንዱ የቆሮስ መስፈሪያ የባዶስን አሥረኛ ክፍል ትሰጣላችሁ፥ አሥር የባዶስ መስፈሪያ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ነውና። 15ውኃም ካለበት ከእስራኤል ማሰማርያ ከመንጋው ከሁለቱ መቶ አንዱን የበግ ጠቦት ትሰጣላችሁ፥ ይህ ያስተሰርይላችሁ ዘንድ ለእህል ቍርባንና ለሚቃጠል መሥዋዕት ለደኅንነትም መሥዋዕት ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይህን መባ ለእስራኤል አለቃ ይሰጣሉ። 17በየበዓላቱም በየመባቻውም በየሰንበታቱም በእስራኤልም ቤት ዓመት በዓል ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የመጠጡንም ቍርባን መስጠት በአለቃው ላይ ይሆናል፥ እርሱ ለእስራኤል ቤት ያስተሰርይ ዘንድ የኃጢአቱን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅነቱን መሥዋዕት ያቀርባል።
18ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ መቅደሱንም አንጻ። 19ካህኑም ከኃጢአቱ መሥዋዕት ደም ወስዶ በመቅደሱ መቃኖችና በመሠዊያው እርከን በአራቱ ማዕዘን በውስጠኛውም አደባባይ በበሩ መቃኖች ላይ ይርጨው። 20ከወሩም በሰባተኛው ቀን እንዲሁ አድርግ፥ ይኸውም ስለ ሳተውና ስላላወቀው ሁሉ ነው። እንዲሁም ስለ ቤቱ አስተስርዩ።
21በመጀመሪያ ወር ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታደርጋላችሁ። እስከ ሰባት ቀንም ድረስ ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ። 22በዚያም ቀን አለቃው ለራሱና ለአገሩ ሕዝብ ሁሉ የኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ያቅርብ። 23በበዓሉም በሰባቱ ቀኖች የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፥ ሰባቱን ቀኖች በየዕለቱ ነውር የሌለባቸውን ሰባት ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ያቅርብ፥ ለኃጢአትም መሥዋዕት በየዕለቱ አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ። 24ለአንድም ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ለእህል ቍርባን ያቅርብ። 25በሰባተኛውም ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በበዓሉ ሰባት ቀኖች፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የእህሉንም ቍርባን ከዘይቱ ጋር እንዲሁ ያቅርብ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 45: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ