ትንቢተ ሆሴዕ 10
10
1እስራኤል ፍሬው የበዛለት የለመለመ ወይን ነው፥ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያውን አብዝቶአል፥ እንደ ምድሩም ማማር መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል። 2ልባቸው ተከፈለ፥ አሁንም በደላቸውን ይሸከማሉ፥ እርሱ መሠዊያቸውን ያፈርሳል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል። 3አሁንም፦ ንጉሥ የለንም፥ እግዚአብሔርን አልፈራንምና፥ ንጉሥስ ምን ያደርግልናል? ይላሉ።
4የማይረባውን ቃል ይናገራሉ፥ ቃል ኪዳን በገቡ ጊዜ በሐሰት ይምላሉ፥ ስለዚህ መርዛም ሣር በእርሻ ትልም ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት ይበቅልባቸዋል። 5የሰማርያ ሰዎች ስለ ቤትአዌን እምቦሳ ይፈራሉ፥ ክብሩም ከእርሱ ዘንድ ወጥቶአልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም በኀዘን ይንተባተባሉ። 6ለንጉሡ ለኢያሪም እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ ወደ አሦር ይማረካል፥ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል። 7ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ ጠፍታለች። 8የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ እሾህና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፥ ተራሮችንም፦ ክደኑን፥ ኮረብቶችንም፦ ውደቁብን ይሉአቸዋል።
9እስራኤል ሆይ፥ ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፥ በዚያ ጸንተዋል፥ በጊብዓ ላይ ሰልፍ አይደርስባቸውምን? 10በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፥ ስለ ሁለቱም ኃጢአታቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ ይሰበሰቡባቸዋል። 11ኤፍሬም ማበራየት እንደ ለመደች ጊደር ነው፥ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፥ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም አፈሩን ያለሰልሳል።
12እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ። 13ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፥ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና። 14በሕዝብህም መካከል ሽብር ይነሣል፥ እናትም ከልጆችዋ ጋር በተፈጠፈጠች ጊዜ ሰልማን ቤትአርብኤልን በሰልፍ ቀን እንዳፈረሰ፥ አምባዎችህ ሁሉ ይፈርሳሉ። 15ከኃጢአታችሁም ክፋት የተነሣ ቤቴል እንዲሁ ያደርግባችኋል፥ በነጋ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 10: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ