ትንቢተ ሆሴዕ 11
11
1እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። 2አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ፥ ለበኣሊምም ይሠው ነበር፥ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር። 3እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ በእግሩ እንዲሄድ መራሁት፥ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። 4በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፥ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው።
5ወደ እኔ ይመለሱ ዘንድ አልወደዱምና ወደ ግብጽ ምድር ይመለሳሉ፥ አሦርም ንጉሣቸው ይሆናል። 6ከመከሩትም ምክር የተነሣ ሰይፍ በከተሞቻቸው ላይ ይወድቃል፥ ከበርቴዎችንም ያጠፋል። 7ሕዝቤም ከእኔ ይመለሱ ዘንድ ወደዱ፥ ወደ ላይም ቢጠሩአቸው ማንም ከፍ ከፍ ያደርጋቸው ዘንድ አይችልም።
8ኤፍሬም ሆይ፥ እንዴት እጥልሃለሁ? እስራኤል ሆይ፥ እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? እንዴትስ እንደ አዳማ እጥልሃለሁ? እንዴትስ እንደ ሲባዩ አደርግሃለሁ? ልቤ በውስጤ ተናውጣለች፥ ምሕረቴም ተነሣሥታለች። 9እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካከልህም ቅዱሱ ነኝና የቁጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፥ ኤፍሬምንም አጠፋ ዘንድ አልመለስም፥ በመዓትም አልመጣም። 10እግዚአብሔርን ይከተላሉ፥ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፥ ባገሣም ጊዜ ልጆች እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ። 11እንደ ወፍም ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር ምድር እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፥ በቤታቸውም አኖራቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 11: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ