ትንቢተ ኢሳይያስ 57

57
1ጻድቅ ይሞታል፥ በልቡም ነገሩን የሚያኖር የለም፥ ምሕረተኞችም ይወገዳሉ፥ ጽድቅም ከክፋት ፊት እንደ ተወገደ ማንም አያስተውልም። 2ወደ ሰላም ይገባል፥ በቅንነት የሄደ በአልጋው ላይ ያርፋል። 3እናንተ የአስማተኛይቱ ልጆች፥ የአምንዝራውና የጋለሞታይቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ። 4በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ? 5እናንተ በአድባር ዛፎች መካከል በለመለመም ዛፍ ሁሉ በታች በፍትወት የምትቃጠሉ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ሕፃናትን የምታርዱ፥ የዓመፅ ልጆችና የሐሰት ዘር አይደላችሁምን? 6በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፥ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፥ የእልንም ቍርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣም? 7ከፍ ባለውም በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፥ መሥዋዕትንም ትሠዊ ዘንድ ወደዚያ ወጣሽ። 8ከመዝጊያውና ከመቃኑ በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፥ እኔን ትተሽ ለሌላ ተገልጠሻል፥ ወጥተሽ መኝታሽን አስፍተሻል፥ ቃል ኪዳንም ተጋባሻቸው፥ ባየሽበትም ስፍራ ሁሉ መኝታቸውን ወደድሽ። 9ዘይትም ይዘሽ ወደ ንጉሡ ሄድሽ፥ ሽቱሽንም አበዛሽ፥ መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፥ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ። 10በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፥ ነገር ግን፦ ተስፋ የለም አላልሽም፥ የጕልበትን መታደስ አገኘሽ፥ ስለዚህም አልዛልሽም። 11ሐሰትን የተናገርሺው እኔንም ያላሰብሽው በልብሽም ነገሩን ያላኖርሺው ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔ ብዙ ጊዜ ዝም አልሁ፥ አንቺም አልፈራሽም። 12እኔ ጽድቅሽን እናገራለሁ፥ ሥራሽም አይረባሽም። 13ወደ አንቺ የሰበሰብሻቸው በጮኽሽ ጊዜ ይታደጉሽ፥ ንፋስ ግን ይወስዳቸዋል ሽውሽውታም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። በእኔ የታመነ ግን ምድሪቱን ይገዛል፥ የተቀሰውንም ተራራዬን ይወርሳል። 14እርሱም፦ ጥረጉ፥ መንገድን አዘጋጁ፥ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አውጡ ይላል። 15ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል፦ የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። 16መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘላለም አልጣላም፥ ሁልጊዜም አልቈጣም። 17-18ስለ ኃጢአቱ ጥቂት ጊዜ ተቆጥቼ ቀሠፍሁት፥ ፊቴን ሰውሬ ተቈጣሁ፥ እርሱም በልቡ መንገድ እያፈገፈገ ሄደ። መንገዱን አይቻለሁ እፈውሰውማለሁ፥ እመራውማለሁ፥ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱ መጽናናትን እመልሳለሁ። 19የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ፥ በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፥ እፈውሰውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 20ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፥ ጸጥ ይል ዘንድ አይችልምና፥ ውኆቹም ጭቃና ጕድፍ ያወጣሉና። 21ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ