መጽሐፈ መሳፍንት 15
15
1ከዚህም በኋላ በስንዴ መከር ጊዜ ሶምሶን የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደና፦ ወደ ጫጉላ ቤት ወደ ሚስቴ ልግባ አለ፥ አባትዋ ግን እንዳይገባ ከለከለው። 2አባትዋም፦ ፈጽመህ የጠላሃት መስሎኝ ለሚዜህ አጋባኋት፥ ታናሽ እኅትዋ ከርስዋ ይልቅ የተዋበች አይደለችምን? እባክህ፥ በእርስዋ ፋንታ አግባት አለው። 3ሶምሶንም፦ ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ባደርግ እኔ ንጹሕ ነኝ አላቸው። 4ሶምሶንም ሄዶ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፥ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፥ በሁለቱም ጅራቶች መካከል አንድ ችቦ አደረገ። 5ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፥ ነዶውንም የቆመውንም እህል ወይኑንም ወይራውንም አቃጠለ። 6ፍልስጥኤማውያንም፦ ይህን ያደረገው ማን ነው? አሉ። እነርሱም፦ ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው አጋብቶበታልና የተምናዊው አማች ሶምሶን ነው አሉ። ፍልስጥኤማያንም ወጥተው ሴቲቱንና አባትዋን በእሳት አቃጠሉ። 7ሶምሶንም፦ እናንተ እንዲሁ ብታደርጉ እኔ እበቀላችኋለሁ፥ ከዚያም በኋላ ዐርፋለሁ አላቸው። 8እርሱም ጭን ጭናቸውን ብሎ በታላቅ አገዳደል መታቸው፥ ወርዶም በኤጣም ዓለት ባለው ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ።
9ፍልስጥኤማውያንም ወጡ፥ በይሁዳም ሰፈሩ፥ በሌሒ ላይም ተበታትነው ተቀመጡ። 10የይሁዳም ሰዎች፦ በእኛ ላይ የወጣችሁት ለምንድር ነው? አሉ። እነርሱም፦ ሶምሶንን ልናስር፥ እንዳደረገብንም ልናደርግበት መጥተናል አሉ። 11ከይሁዳም ሰዎች ሦስት ሺህ የሚያህሉ በኤጣም ዓለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሶምሶንን፦ ገዦቻችን ፍልስጥኤማውያን እንደ ሆኑ አታውቅምን? ያደረግህብን ይህ ምንድር ነው? አሉት። እርሱም፦ እንዳደረጉብኝ እንዲሁ አደረግሁባቸው አላቸው። 12እነርሱም፦ አስረን በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፈን ልንሰጥህ መጥተናል አሉት። ሶምሶንም፦ እናንተ እንዳትገሉኝ ማሉልኝ አላቸው። 13እነርሱም፦ አስረን በእጃቸው አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ አንገድልህም ብለው ተናገሩት። በሁለትም አዲስ ገመድ አስረው ከዓለቱ ውስጥ አወጡት።
14ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን እልል እያሉ ተገናኙት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፥ ክንዱም የታሰረበት ገመድ በእሳት እንደ ተበላ እንደ ተልባ እግር ፈትል ሆነ፥ ማሰሪያዎቹም ከእጁ ወደቁ። 15አዲስም የአህያ መንጋጋ አገኘ፥ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው፥ በእርሱም አንድ ሺህ ሰው ገደለ። 16ሶምሶንም፦ በአህያ መንጋጋ ክምር በክምር ላይ አድርጌአቸዋለሁ፥ በአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰው ገድያለሁ አለ። 17መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ መንጋጋውን ከእጁ ጣለ፥ የዚያንም ስፍራ ስም ራማትሌሒ ብሎ ጠራው። 18እርሱም እጅግ ተጠምቶ ነበርና፦ አንተ ይህችን ታላቅ ማዳን በባሪያህ እጅ ሰጥተሃል፥ አሁንም በጥም እሞታለሁ፥ ባልተገረዙትም እጅ እወድቃለሁ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 19እግዚአብሔርም በሌሒ ያለውን አዘቅት ሰነጠቀ፥ ከእርሱም ውኃ ወጣ፥ እርሱም ጠጣ፥ ነፍሱም ተመለሰች፥ ተጠናከረም። ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ዓይንሀቆሬ ብሎ ጠራው፥ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ በሌሒ አለ። 20በፍልስጥኤማውያንም ዘመን በእስራኤል ላይ ሀያ ዓመት ፈረደ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 15: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ