መጽሐፈ ኢያሱ 13
13
1ኢያሱም ሸመገለ በዕድሜም አረጀ፥ እግዚአብሔርም አለው፦ አንተ ሸመገልህ፥ በዕድሜህም አረጀህ፥ ያልተወረሰች እጅግ ብዙ ምድር ገና ቀርታለች፥ 2የቀረችውም ምድር ይህች ናት፥ የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ፥ 3በግብፅ ፊት ካለው ከሺሖር ወንዝ ጀምሮ በሰሜን በኩል እስካለችው የከነዓናውያን ሆና እስከ ተቈጠረችው እስከ አቃሮን ዳርቻ ድረስ፥ የጋዛ፥ የአዛጦን፥ የአስቀሎና፥ የጌት፥ የአቃሮን፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ 4በደቡብም በኩል የኤዋውያን፥ የከነዓናውያን ምድር ሁሉ፥ ለሲዶናውያንም የምትሆን መዓራ እስከ አሞራውያን ዳርቻ እስከ አፌቅ ድረስ፥ 5የጌባላውያንም ምድር፥ በምሥራቅም በኩል ከአርሞንዔም ተራራ በታች ካለችው በኣልጋድ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ያለችው ሊባኖስ ሁሉ፥ 6በተራራማውም አገር የሚኖሩትን ሁሉ ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ማሴሮን ድረስ ሲዶናውያን ሁሉ፥ እነዚህን ከእስራኤል ልጆች ፊት አባርራቸዋለሁ፥ እንዳዘዝሁህም ምድራቸውን ለእስራኤል ርስት አድርገህ አካፍላቸው። 7አሁንም ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገድ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ ክፈለው።
8የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንደ ሰጣቸው ከእርሱ ከምናሴ ጋር የሮቤልና የጋድ ልጆች በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀበሉ። 9በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር፥ በሸለቆውም መካከል ካለችው ከተማ ጀምሮ የሜድባን ሜዳ ሁሉ እስከ ዲቦን ድረስ፥ 10በሐሴቦንም የነገሠ የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተሞች ሁሉ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥ 11ገለዓድንም፥ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ዳርቻ ሁሉ፥ የአርሞንዔምንም ተራራ ሁሉ፥ 12ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ፥ በባሳን የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የዐግን መንግሥት ሁሉ፥ እርሱም ከራፋይም የቀረ ነበረ፥ እነዚህንም ሙሴ መታቸው አወጣቸውም። 13የእስራኤል ልጆች ግን ጌሹራውያንንና ማዕካታውያንን አላወጡም፥ እስከ ዛሬም ድረስ ጌሹርና ማዕካት በእስራኤል መካከል ይኖራሉ። 14ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር የቀረበው በእሳት የተደረገ መሥዋዕት ርስታቸው ነው፥ እርሱ እንደ ተናገራቸው።
15ሙሴም ለሮቤል ልጆች ነገድ በየወገናቸው ርስትን ሰጣቸው። 16ድንበራቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ በሸለቆው መካከል ያለችው ከተማ፥ የሜድባ ሜዳ ሁሉ፥ 17ሐሴቦንም፥ በሜዳውም ያሉት ከተሞችዋ ሁሉ፥ ዲቦን፥ ባሞትበኣል፥ 18ቤትባኣልምዖን፥ ያሀጽ፥ ቅዴሞት፥ 19ሜፍዓት፥ ቂርያታይም፥ ሴባማ፥ በሸለቆውም ተራራ ያለችው ጼሬትሻሐር፥ 20ቤተ ፌጎር፥ ከፈስጋ ተራራ በታች ያለው ምድር፥ ቤትየሺሞት፥ 21የሜዳውም ከተሞች ሁሉ፥ በሐሴቦንም የነገሠው የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ሁሉ ነበረ፥ ሙሴም እርሱንና በምድሪቱ የተቀመጡትን የሴዎንን መሳፍንት፥ የምድያምን አለቆች ኤዊን፥ ሮቆምን፥ ሱርን፥ ሑርን፥ ሪባን መታቸው። 22ከገደሉአቸውም ሰዎች ጋር የእስራኤል ልጆች ምዋርተኛውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን በሰይፍ ገደሉት። 23የሮቤልም ልጆች ድንበር የዮርዳኖስ ወንዝና ዳርቻው ነበረ። የሮቤል ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
24ሙሴም ለጋድ ነገድ ለጋድም ልጆች በየወገኖቻቸው ርስት አድርጎ ሰጣቸው። 25ድንበራቸውም ኢያዜርና የገለዓድ ከተሞች ሁሉ፥ የአሞንም ልጆች ምድር እኩሌታ በረባት ፊት እስካለችው እስከ አሮዔር ድረስ፥ 26ከሐሴቦን ጀምሮ እስከ ራማት ምጽጴ፥ እስከ ብጦኒም ድረስ፥ ከመሃናይም ጀምሮ እስከ ዳቤር ዳርቻ ድረስ፥ 27በሸለቆውም ቤትሀራም፥ ቤትኒምራ፥ ሱኮት፥ ጻፎን፥ የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ቅሬታ ነበረ። ድንበሩም ዮርዳኖስና በምሥራቅ በኩል ባለው በዮርዳኖስ ማዶ የኪኔሬት ባሕር ወዲያኛው ዳርቻ ነበር። 28የጋድ ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
29ሙሴም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት ሰጣቸው፥ ለምናሴም ልጆች ነገድ እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። 30ድንበራቸውም ከመሃናይም ጀምሮ የባሳን ንጉሥ የዐግ መንግሥት፥ ባሳን ሁሉ፥ በባሳንም ያሉት የኢያዕር መንደሮች ሁሉ ስድሳው ከተሞች፥ የገለዓድም እኩሌታ፥ 31በባሳንም ያሉት የዐግ መንግሥት ከተሞች፥ አስታሮትና ኤድራይ ነበረ። እነዚህም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ልጆች ሆኑ፥ ለማኪር ልጆች እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
32ሙሴ በምሥራቅ በኩል በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የከፈለው ርስት ይህ ነው። 33ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳላቸው ርስታቸው እርሱ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 13: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ