መጽሐፈ ኢያሱ 2
2
1የነዌም ልጅ ኢያሱ፦ ሄዳችሁ ምድሪቱንና ኢያሪኮን እዩ ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ። ሄዱም፥ ረዓብም ወደሚሉአት ጋለሞታ ቤት ገቡ፥ በዚያም አደሩ። 2የኢያሪኮም ንጉሥ፦ እነሆ፥ ሰዎች ከእስራኤል ልጆች አገሩን ሊሰልሉ ወደዚህ በሌሊት ገቡ ሲባል ወሬ ሰማ። 3የኢያሪኮም ንጉሥ፦ አገሩን ሁሉ ሊሰልሉ መጥተዋልና ወደ አንቺ የመጡትን ወደ ቤትሽም የገቡትን ሰዎች አውጪ ብሎ ወደ ረዓብ ላከ። 4ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፥ እርስዋም፦ አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፥ ከወዴት እንደሆኑ ግን አላወቅሁም፥ 5በሩም ሲዘጋ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፥ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፥ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፥ ታገኙአቸውማላችሁ አለች። 6እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታቸው ነበር፥ በዚያም በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። 7ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ በሚወስደው መንገድ አሳደዱአቸው፥ አሳዳጆችም ከወጡ በኋላ በሩ ተቈለፈ።
8እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። 9ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፦ እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ እናንተንም መፍራት በላያችን እንደ ወደቀ፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ እንደ ቀለጡ አወቅሁ። 10ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። 11ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም። 12አሁንም፥ እባካችሁ፥ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፥ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፥ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ ሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድትሠሩ፥ 13አባቴንና እናቴንም ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ እንድታድኑ፥ ሰውነታችንንም ከሞት እንድታድኑ። 14ሰዎቹም፦ ይህን ነገራችንን ባትገልጪ ነፍሳችን በነፍሳችሁ ፋንታ ለሞት ይሆናል፥ እግዚአብሔርም ምድሪቱን በሰጠን ጊዜ ከአንቺ ጋር ቸርነትንና እውነትን እናደርጋለን አሉአት።
15ቤትዋም በከተማ ቅጥር የተጠጋ ነበረና፥ እርስዋም በቅጥሩ ላይ ተቀምጣ ነበረና ከመስኮቱ በገመድ አወረደቻቸው። 16እርስዋም፦ አሳዳጆቹ እንዳያገኙአችሁ ወደ ተራራው ሂዱ፥ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ በዚያ ሦስት ቀን ተሰውራችሁ ተቀመጡ፥ ኋላም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ አለቻቸው። 17ሰዎቹም አሉአት፦ እኛ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። 18እነሆ፥ እኛ ወደ አገሩ በገባን ጊዜ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል እሰሪው፥ አባትሽንም እናትሽንም ወንድሞችሽንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ ሁሉ ወደ አንቺ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ። 19ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፥ እኛም ንጹሐን እንሆናለን፥ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤቱ ውስጥ ያለውን አንድ እጅ ቢነካው ደሙ በእኛ ራስ ላይ ይሆናል። 20ይህንን ነገራችንን ግን ብትገልጪ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። 21እርስዋም፦ እንደ ቃላችሁ ይሁን አለች፥ ሰደደቻቸውም እነርሱም ሄዱ፥ ቀዩንም ፈትል በመስኮቱ በኩል አንጠለጠለችው።
22እነርሱም ሄደው ወደ ተራራው ደረሱ፥ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጡ፥ አሳዳጆቹም በመንገዱ ሁሉ ፈልገው አላገኙአቸውም። 23ሁለቱም ሰዎች ተመለሱ፥ ከተራራውም ወርደው ተሻገሩ፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ፥ የደረሰባቸውንም ሁሉ አወሩለት። 24ኢያሱንም፦ በእውነት እግዚአብሔር አገሩን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአል፥ በአገሩም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በፊታችን ይቀልጣሉ አሉት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 2: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ