የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 25

25
1እስራኤልም በሰጢም ተቀመጡ፤ ሕዝቡም ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዝሩ ጀመር። 2ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ወደ አምላኮቻቸውም ሰገዱ። 3እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ። 4እግዚአብሔርም ሙሴን፦ የእግዚአብሔር የቍጣው ጽናት ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐዩ ፊት ወደ እግዚአብሔር ስቀላቸው አለው። 5ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች፦ እናንተ ሁሉ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ አላቸው። 6እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ በሙሴና በእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ፊት ምድያማዊቱን አንዲቱን ሴት ወደ ወንድሞቹ አመጣት፤ እነርሱም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያለቅሱ ነበር። 7የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ፤ 8ያንንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። እስራኤላዊውንም ሰውና ሴቲቱን ሁለቱን ሆዳቸውን ወጋቸው። ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተከለከለ። 9በመቅሠፍትም የሞተው ሀያ አራት ሺህ ነበረ። 10እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 11የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቍጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም። 12ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሰላሜን ቃል ኪዳን እሰጠዋለሁ። 13ለአምላኩም ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል። 14ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ነበረ፤ የአባቱ ቤት አለቃ የስምዖናውያን የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ። 15የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ነበረ፤ እርስዋም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም በምድያም ዘንድ የአባቱ ቤት ወገን አለቃ ነበረ። 16እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 17-18በፌጎር በመቅሠፍቱ ቀን ስለተገደለችው ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሸነገሉአችሁ ሽንገላ አስጨንቀዋችኋልና ምድያማውያንን አስጨንቁአቸው ግደሉአቸውም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ