የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 14

14
ጳውሎስና በርናባስ በኢቆንዮን
1በኢቆንዮንም ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ በዚያም በሚገባ ስላስተማሩ፣ ከአይሁድም ከግሪክም እጅግ ብዙ ሰዎች አመኑ። 2ያላመኑት አይሁድ ግን፣ አሕዛብን አነሣሥተው ወንድሞችን እንዲጠሉ አደረጓቸው። 3ጳውሎስና በርናባስም ስለ ጌታ በድፍረት እየተናገሩ ብዙ ጊዜ እዚያው ቈዩ፤ ጌታም የሚናገሩትን የጸጋውን ቃል በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ሥራ እየደገፈ ያረጋግጥላቸው ነበር። 4የከተማውም ሕዝብ ተከፋፈለ፤ ገሚሱ ከአይሁድ ጋር፣ ገሚሱም ከሐዋርያት ጋር ሆነ። 5በዚህ ጊዜ አሕዛብና አይሁድ ከመሪዎቻቸው ጋር ተባብረው ሊያንገላቷቸውና በድንጋይ ሊያስወግሯቸው ሞከሩ። 6እነርሱ ግን ይህን እንዳወቁ ልስጥራንና ደርቤን ወደተባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሹ፤ 7በዚያም ወንጌልን መስበክ ቀጠሉ።
ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራና በደርቤን
8በልስጥራንም፣ እግሩ ዐንካሳ የሆነና ከተወለደ ጀምሮ ፈጽሞ በእግሩ ሄዶ የማያውቅ ሽባ ሰው ተቀምጦ ነበር። 9ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ያደምጥ ነበር። ጳውሎስም ወደ እርሱ ትኵር ብሎ ተመለከተና ለመዳን እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ 10በታላቅ ድምፅ፣ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም!” አለው፤ በዚህ ጊዜ ዘልሎ ተነሣና መራመድ ጀመረ።
11ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፣ በሊቃኦንያ ቋንቋ፣ “አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ጮኹ፤ 12በርናባስን “ድያ” አሉት፤ ጳውሎስም ዋና ተናጋሪ ስለ ነበር “ሄርሜን” አሉት። 13ከከተማው ወጣ ብሎ የነበረው የድያ ቤተ መቅደስ ካህንም፣ ኰርማዎችንና የአበባ ጕንጕኖችን ወደ ከተማው መግቢያ አምጥቶ፣ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ፈለገ።
14ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቡ መካከል ሮጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ 15“እናንት ሰዎች፤ ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እኮ እንደ እናንተው ሰዎች ነን። እናንተም ደግሞ ከዚህ ከንቱ ነገር ርቃችሁ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር እንድትመለሱ ወንጌልን እንሰብክላችኋለን። 16እርሱ ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በገዛ መንገዳቸው እንዲሄዱ ተዋቸው፤ 17ይሁን እንጂ ዝናብን ከሰማይ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠቱ፣ ደግሞም ልባችሁን በመብልና በደስታ በማርካቱ መልካምን በማድረግ ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” 18ይህን ሁሉ ተናግረው እንኳ፣ ሕዝቡ እንዳይሠዋላቸው ያስተዉት በብዙ ችግር ነበር።
19አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጥተው፣ ሕዝቡን አግባቡ፤ ጳውሎስንም በድንጋይ ከወገሩት በኋላ፣ የሞተ መስሏቸው ጐትተው ከከተማው ወደ ውጭ አወጡት። 20ሆኖም ደቀ መዛሙርት ከብበውት እንዳሉ ተነሣ፤ ወደ ከተማም ገባ። በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ሄዱ።
ጳውሎስና በርናባስ በሶርያ ወዳለችው አንጾኪያ ተመለሱ
21ጳውሎስና በርናባስ በደርቤን የምሥራቹን ቃል ሰብከው፣ ብዙ ደቀ መዛሙርትም ካፈሩ በኋላ፣ ወደ ልስጥራን፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። 22የደቀ መዛሙርቱንም ልብ በማበረታታትና በእምነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ በመምከር፣ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ማለፍ አለብን” አሏቸው። 23ከዚያም በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ፣ በጾምና በጸሎት ላመኑበት ጌታ ዐደራ ሰጧቸው። 24በጲስድያም ዐልፈው ወደ ጵንፍልያ መጡ፤ 25በጴርጌንም ቃሉን ከሰበኩ በኋላ፣ ወደ አጣልያ ወረዱ።
26ከአጣልያም፣ እስካሁን ላከናወኑት ሥራ፣ ለእግዚአብሔር ጸጋ በዐደራ ወደ ተሰጡባት ከተማ ወደ አንጾኪያ በመርከብ ተመለሱ። 27እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ ቤተ ክርስቲያንን በአንድነት ሰብስበው፣ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት ያደረገውን ሁሉ፣ ደግሞም ለአሕዛብ እንዴት የእምነትን በር እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ። 28በዚያም ከደቀ መዛሙርት ጋር ብዙ ጊዜ ተቀመጡ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ