የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 6

6
የሰባቱ ዲያቆናት መመረጥ
1የደቀ መዛሙርት ቍጥር እየጨመረ በሄደበት በዚህ ወቅት፣ ከግሪክ አገር የመጡ አይሁድ በይሁዳ ይኖሩ በነበሩት አይሁድ ላይ አጕረመረሙ፤ ምክንያቱም በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማደል አሠራር ላይ ከእነርሱ ወገን የሆኑት መበለቶች ችላ ተብለው ነበር። 2ስለዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሌሎችን ደቀ መዛሙርት በአንድነት ሰብስበው እንዲህ አሉ፤ “እኛ የማእዱን አገልግሎት ለማስተናገድ ስንል የእግዚአብሔርን ቃል አገልግሎት መተው አይገባንም። 3ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ መካከል በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች ምረጡ፤ ይህን ኀላፊነት ለእነርሱ እንሰጣለን፤ 4እኛ ግን በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት እንተጋለን።”
5አባባሉ ሁላቸውን ደስ አሰኘ፤ በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን እስጢፋኖስን እንዲሁም ፊልጶስን፣ ጵሮኮሮስን፣ ኒቃሮናን፣ ጢሞናን፣ ጰርሜናንና ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን አንጾኪያዊውን ኒቆላዎስን መረጡ። 6እነዚህንም አምጥተው ሐዋርያት ፊት አቀረቧቸው፤ እነርሱም ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው።
7የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፤ የደቀ መዛሙርቱም ቍጥር በኢየሩሳሌም እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙዎቹ ለእምነት የታዘዙ ሆኑ።
የእስጢፋኖስ መያዝ
8በዚህ ጊዜ እስጢፋኖስ ጸጋንና ኀይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን ያደርግ ነበር። 9“የነጻ ወጪዎች ምኵራብ” ተብሎ የሚጠራው ምኵራብ አባላት የሆኑ ከቀሬናና ከእስክንድርያ፣ እንዲሁም ከኪልቅያና ከእስያ አውራጃዎች የመጡ ሰዎችም ተቃውሞ አስነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ጀመር፤ 10ይሁን እንጂ ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም።
11ስለዚህ፣ “እስጢፋኖስ በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ሲሰነዝር ሰምተናል” የሚሉ ሰዎችን በስውር አዘጋጁ።
12በዚህ ሁኔታ ሕዝቡን፣ የአገር ሽማግሌዎቹንና የሕግ መምህራኑን በማነሣሣት፣ እስጢፋኖስን አስይዘው በአይሁድ ሸንጎ ፊት አቀረቡት፤ 13እንዲህ ብለው የሚመሰክሩ የሐሰት ምስክሮችንም አቆሙበት፤ “ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራና በሕጉ ላይ የስድብ ቃል መናገሩን በፍጹም አልተወም፤ 14ምክንያቱም ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ እንደሚያጠፋና ከሙሴ የተቀበልነውን ወግ እንደሚለውጥ ሲናገር ሰምተነዋል።”
15በሸንጎው ተቀምጠው የነበሩትም ሁሉ እስጢፋኖስን ትኵር ብለው ሲመለከቱት ፊቱ የመልአክ ፊት መስሎ ታያቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ