ዘፍጥረት 23
23
የሣራ ሞት
1ሣራ አንድ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ኖረች፤ 2በከነዓን ምድር፣ በቂርያት አርባቅ ማለትም በኬብሮን ከተማ ሞተች፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያለቅስና ሊያዝን መጣ።
3ከዚያም አብርሃም ከተቀመጠበት ከሚስቱ ሬሳ አጠገብ ተነሣ፤ ኬጢያውያንንም#23፥3 ወይም የኬጢ ልጆች፤ 5፡7፡10፡16፡18 እና 20 እንዲሁ እንዲህ አላቸው፤ 4“እኔ ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ ሆኜ በመካከላችሁ የምኖር ነኝና ለመቃብር የምትሆን ቦታ ሽጡልኝ፤ የሚስቴንም ሬሳ ልቅበርበት።”
5ኬጢያውያንም ለአብርሃም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ 6“ስማን ጌታዬ፤ አንተ እኮ በእኛ ዘንድ እንደ ኀያል መስፍን ነህ፤ ከመቃብር ቦታችን በመረጥኸው ስፍራ ሬሳህን መቅበር ትችላለህ፤ ማናችንም ብንሆን የሞተብህን ሰው እንዳትቀብርበት የመቃብር ቦታችንን አንከለክልህም።”
7ከዚያም አብርሃም ተነሥቶ የአገሬውን ሕዝብ፣ ኬጢያውያንን እጅ ነሣ፤ 8እንዲህም አላቸው፤ “እንድቀብር ከፈቀዳችሁልኝ፣ አንዴ ስሙኝና የሰዓርን ልጅ ኤፍሮንን ስለ እኔ ሆናችሁ ለምኑልኝ። 9ይኸውም በዕርሻው ድንበር ላይ ያለችውን መክፈላ የተባለችውን ዋሻውን እንዲሸጥልኝ ነው፤ በመካከላችሁም የመቃብር ቦታ እንድትሆነኝ በሙሉ ዋጋ እንዲሸጥልኝ ለምኑልኝ።”
10ኬጢያዊው ኤፍሮንም እዚያው መካከላቸው ተቀምጦ ስለ ነበር፣ ወደ ከተማው በር መግቢያ መጥተው የተሰበሰቡት ኬጢያውያን በሙሉ እየሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ 11“እንዲህ አይደለም ጌታዬ፤ አድምጠኝ፤ ዕርሻውን በውስጡ ካለው ዋሻ ጋር ውሰደው። እነሆ፤ በወገኖቼ ኬጢያውያን ፊት ሰጥቼሃለሁ፤#23፥11 ወይም ሸጬልሃለሁ ሬሳህን ቅበርበት።”
12አብርሃም እንደ ገና የአገሬውን ሕዝብ እጅ ነሣና 13ሁሉም እየሰሙት፣ “የዕርሻውን ቦታ ዋጋ ልክፈል፤ እባክህን ተቀበለኝና ሬሳዬን ልቅበርበት” አለው።
14ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ 15“ጌታዬ ስማኝ፤ የመሬቱ ዋጋማ አራት መቶ ጥሬ ብር#23፥15 4.5 ኪሎ ግራም ገደማ ይሆናል ነው፤ ታዲያ ይህ በእኔና በአንተ መካከል ምን ቁም ነገር አለው? ይልቅስ ሬሳህን ቅበርበት” አለው።
16አብርሃምም፣ ኤፍሮን በኬጢያውያን ፊት በተናገረው ዋጋ ተስማማ፤ በወቅቱም የንግድ መለኪያ መሠረት አራት መቶ ጥሬ ብር መዘነለት።
17በዚህ ሁኔታ፣ በመምሬ አጠገብ በመክፈላ ያለው የኤፍሮን ዕርሻ ቦታ ከነዋሻው በክልሉ ካሉት ዛፎች ሁሉ ጭምር ለአብርሃም በርስትነት ተላለፈ፤ 18ወደ ከተማው በር በመጡት ኬጢያውያንም ሁሉ ፊት የአብርሃም ንብረት መሆኑም ተረጋገጠለት። 19ከዚህም በኋላ አብርሃም በከነዓን ምድር፣ በመምሬ አጠገብ፣ መክፈላ በተባለች ዕርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ የሚስቱን የሣራን ሬሳ ቀበረ፤ ይህችም ኬብሮን ናት። 20ስለዚህ ዕርሻውና ውስጡ የሚገኘው ዋሻ የመቃብር ቦታ እንዲሆን ከኬጢያውያን ለአብርሃም በርስትነት ተላለፈለት።
Currently Selected:
ዘፍጥረት 23: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.