ሉቃስ 10
10
ኢየሱስ ሰባ ሁለቱን ላካቸው
10፥4-12 ተጓ ምብ – ሉቃ 9፥3-5
10፥13-15፡21፡22 ተጓ ምብ – ማቴ 11፥21-23፡25-27
10፥23፡24 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥16፡17
1ከዚህ በኋላ ጌታ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መርጦ ሾመ፤ ወደሚሄድበትም ከተማና ቦታ ሁሉ እንዲቀድሙት፣ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ 2እንዲህም አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂት ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ ቦታ እንዲልክ ለምኑት። 3እንግዲህ ሂዱ፤ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። 4ኰረጆ ወይም ከረጢት ወይም ጫማ አትያዙ፤ በመንገድ ላይም ለማንም ሰላምታ አትስጡ።
5 “ወደ ማንኛውም ቤት ስትገቡ አስቀድማችሁ፣ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን’ በሉ፤ 6የሰላም ሰው በዚያ ካለ፣ ሰላማችሁ ያርፍበታል፤ አለዚያም ሰላማችሁ ለእናንተው ይመለሳል። 7ያቀረቡላችሁን ሁሉ እየበላችሁና እየጠጣችሁ በዚያ ቤት ተቀመጡ፤ የሚሠራ ደመወዝ ማግኘት ይገባዋልና። ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት አትዘዋወሩ።
8 “ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ ከተቀበሏችሁ፣ ያቀረቡላችሁን ብሉ። 9በዚያ የሚገኙትን በሽተኞች እየፈወሳችሁ፣ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች’ በሏቸው። 10ነገር ግን ወደ አንድ ከተማ ገብታችሁ ካልተቀበሏችሁ፣ ወደ አደባባዩ ውጡና እንዲህ በሉ፤ 11‘በእግራችን ላይ ያለውን የከተማችሁን ትቢያ እንኳ እናራግፍላችኋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች ይህን ዕወቁ።’ 12እላችኋለሁ፤ በዚያን ዕለት ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ቀላል ይሆንላታል።
13 “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ በእናንተ የተደረጉት ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር። 14ነገር ግን በፍርድ ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። 15አንቺም ቅፍርናሆም፣ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል#10፥15 ወይም ወደ ጥልቁ ትወርጃለሽ።
16 “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።”
17ሰባ ሁለቱም ደስ እያላቸው ተመልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት።
18እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። 19እንግዲህ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፣ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም አንዳች ነገር አይኖርም። 20ይሁን እንጂ መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”
21በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ሁሉ ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፣ አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና።
22 “ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ደግሞም ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብ ማን እንደ ሆነም ከወልድ በቀር፣ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ የለም።”
23ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፤ 24እላችኋለሁና፤ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ፈልገው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ለመስማት ፈልገው አልሰሙም።”
ደጉ ሳምራዊ
10፥25-28 ተጓ ምብ – ማቴ 22፥34-40፤ ማር 12፥28-31
25እነሆም አንድ ቀን፣ አንድ ሕግ ዐዋቂ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነሥቶ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” አለው።
26ኢየሱስም፣ “በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነብበዋለህ?” ሲል መለሰለት።
27ሰውየውም መልሶ፣ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ ይላል” አለው።
28ኢየሱስም፣ “በትክክል መልሰሃል፤ አንተም እንደዚሁ አድርግ፤ በሕይወት ትኖራለህ” አለው።
29ሰውየውም ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፣ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” አለው።
30ኢየሱስም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠው፤ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በወንበዴዎች እጅ ወደቀ፤ ልብሱንም ገፍፈው ደበደቡት፤ በሞት አፋፍ ላይ ጥለውት ሄዱ። 31አንድ ካህን በአጋጣሚ በዚያው መንገድ ቍልቍል ሲወርድ አየውና ገለል ብሎ ዐለፈ። 32ደግሞም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና እርሱም ገለል ብሎ ዐለፈ። 33አንድ ሳምራዊ ግን እግረ መንገዱን ሲሄድ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ ዐዘነለት፤ 34ቀርቦም ቍስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት፤ በራሱም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም ተንከባከበው። 35በማግስቱም ሁለት ዲናር#10፥35 ወይም ሁለት የናስ ሳንቲሞች አውጥቶ ለማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠና፣ ‘ይህን ሰው ዐደራ አስታምመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውንም ወጭ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው።
36 “እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?”
37ሕግ ዐዋቂውም፣ “የራራለት ነዋ” አለ።
ኢየሱስም፣ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።
ኢየሱስ በማርታና በማርያም ቤት
38ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ መንገድ ሲሄዱ፣ ኢየሱስ ወደ አንድ መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤቷ ተቀበለችው። 39እርሷም ማርያም የተባለች እኅት ነበረቻት፤ ማርያምም ቃሉን እየሰማች በጌታ እግር ሥር ተቀምጣ ነበር። 40ማርታ ግን በሥራ ብዛት ትባክን ነበርና ወደ እርሱ ቀርባ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኅቴ ሥራውን ለእኔ ብቻ ጥላ ስትቀመጥ ዝም ትላለህን? እንድታግዘኝ ንገራት እንጂ” አለችው።
41ጌታ ግን እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ማርታ፣ ማርታ፤ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፤ ትዋከቢአለሽም፤ 42የሚያስፈልገው ግን አንድ ነገር ብቻ ነው#10፥42 አንዳንድ ቅጆች የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ብቻ ነው ይላሉ።፤ ማርያም እኮ የሚሻለውን ድርሻ መርጣለች፤ ይህም ከእርሷ አይወሰድም።”
Currently Selected:
ሉቃስ 10: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.