አሞጽ 9:13-14
አሞጽ 9:13-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እነሆ፥ እንዲህ ያለ ወራት ይመጣልን? ይላል እግዚአብሔር፤ እርሻ ከአጨዳ ጋር፥ ዘርም ከእሸት ጋር አንድ ይሆናል፤ ከተራሮችም ማር ይፈስሳል፤ ኮረብታውም ይለመልማል። የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ የወይን ጠጃቸውንም ይጠጣሉ፤ ተክልን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።
አሞጽ 9:13-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ዐጫጁ ዐጭዶ ሳይጨርስ፣ ዐራሹ በላዩ የሚደርስበት፣ ችግኝ ተካዩም ገና ተክሎ ሳይጨርስ፣ ወይን ጨማቂው የሚደርስበት ጊዜ ይመጣል፤ አዲስ የወይን ጠጅ ከተራሮች ይንጠባጠባል፤ ከኰረብቶችም ሁሉ ይፈስሳል። የተሰደደውን ሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ።
አሞጽ 9:13-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚያገኝበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ተራሮችም በተሀውን የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ። የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፥ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፥ አታክልትንም ያባጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ።
አሞጽ 9:13-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእህል ሰብል አጫጆች አጭደው ሳይጨርሱ፥ አራሾች የሚደርሱባቸውና ወይን ጨማቂዎችም የወይን ፍሬ ጨምቀው ሳይጨርሱ፥ የወይን ተካዮች የሚደርሱባቸው ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ተራራዎች ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያፈልቃሉ፤ ኰረብቶችም በወይን ጠጅ ይጥለቀለቃሉ። ሕዝቤን እስራኤልን ወደ አገራቸው መልሼ አመጣለሁ፤ የፈረሱትን ከተሞች እንደገና ሠርተው በዚያ ይኖራሉ፤ ወይን ተክለው የወይን ጠጅ ይጠጣሉ፤ ልዩ ልዩ ተክሎችን ተክለው ፍሬውን ይመገባሉ።