ዮሐንስ 18:28-38
ዮሐንስ 18:28-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ፍርድ አደባባይ ወሰዱት፤ አይሁድ ግን ፈጽሞ ስለ ነጋ የፋሲካውን በግ ሳይበሉ እንዳይረክሱ ወደ ፍርድ አደባባይ አልገቡም። ጲላጦስም ወደ እነርሱ ወደ ውጭ ወጥቶ፥ “ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደሉ ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም፥ “ክፉ የሠራ ባይሆንስ ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነው ነበር” ብለው መለሱለት። ጲላጦስም፥ “እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው፤ አይሁድም፥ “እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም” አሉት። ይህም በምን ዐይነት ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው የጌታችን የኢየሱስ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ጲላጦስም እንደገና ወደ ፍርድ አደባባይ ገብቶ ጌታችን ኢየሱስን ጠራና፥ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ይህን የምትናገር ከራስህ ነውን? ወይስ ስለ እኔ የነገረህ ሌላ አለን?” ብሎ መለሰለት። ጲላጦስም መልሶ፥ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ ወገኖችህና ሊቃነ ካህናት አይደሉምን? Aረ ምን አድርገሃል?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ በዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ ለአይሁድ እንዳልሰጥ አሽከሮች በተዋጉልኝ ነበር፤ አሁንም መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” ብሎ መለሰለት። ጲላጦስም፥ “እንግዲያ አንተ ንጉሥ ነህን?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ራስህ ትላለህ፤ እኔ ስለዚህ ተወለድሁ፤ ስለዚህም ለእውነት ልመሰክር ወደ ዓለም መጣሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ቃሌን ይሰማኛል” አለው። ጲላጦስም፥ “እውነት ምንድነው?” አለው፤ ይህንም ተናግሮ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጣና እንዲህ አላቸው፥ “እኔ አንዲት ስንኳን በደል አላገኘሁበትም።
ዮሐንስ 18:28-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አይሁድም ኢየሱስን ከቀያፋ ወደ ሮማዊው ገዥ ግቢ ይዘውት ሄዱ፤ ጊዜውም ማለዳ ነበር። አይሁድም ፋሲካን መብላት እንዲችሉ፣ ላለመርከስ ወደ ገዥው ግቢ አልገቡም። ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጥቶ፣ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ይህ ሰው ወንጀለኛ ባይሆን ኖሮ፣ አንተ ፊት ባላቀረብነውም ነበር” ብለው መለሱለት። ጲላጦስም፣ “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም፣ “እኛማ በማንም ላይ የሞት ፍርድ ለመፍረድ መብት የለንም” አሉት። ይህ የሆነው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ጲላጦስም ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን አስጠራና፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ይህ ሐሳብ የራስህ ነው? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ የነገሩህ?” ሲል መለሰለት። ጲላጦስም መልሶ፣ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወደ እኔ የላኩህ የራስህ ወገኖችና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ለመሆኑ ምን አድርገህ ነው?” አለው። ኢየሱስም፣ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ አገልጋዮቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” አለው። ጲላጦስም፣ “ታዲያ፣ ንጉሥ ነህ ማለት ነዋ!” አለው። ኢየሱስም፣ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል” አለው። ጲላጦስም፣ “እውነት ምንድን ነው?” አለው፤ ይህን ከተናገረ በኋላም እንደ ገና ወደ አይሁድ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ የሚያስከስስ በደል አላገኘሁበትም፤
ዮሐንስ 18:28-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየስስንም ከቀያፋ ወደ ገዡ ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም የፋሲካ በግ ይበሉ ዘንድ እንጂ እንዳይረክሱ ወደ ገዡ ግቢ አልገቡም። ስለዚህ ጲላጦስ ወደ ውጭ ወደ እነርሱ ወጥቶ፦ “ይህን ሰው ስለ ምን ትከሱታላችሁ” አላቸው። እነርሱም መልሰው፦ “ይህስ ክፉ አድራጊ ባይሆን ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” አሉት። ጴላጦስም፦ “እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም፦ “ለእኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም” አሉት፤ ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት ሊሞት እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ጲላጦስም እንደ ገና ወገ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ፦ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን?” አለው። ጲላጦስ መልሶ፦ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” አለው። ጲላጦስም፦ “እንግዲያ ንጉሥ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” አለው። ጲላጦስ፦ “እውነት ምንድር ነው?” አለው። ይህንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጥቶ፦ “እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም።
ዮሐንስ 18:28-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ከቀያፋ ቤት ወደ አገረ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ጊዜውም ጠዋት ማለዳ ነበር፤ አይሁድ ለፋሲካ በዓል የሚታረደውን በግ መብላት ስለ ነበረባቸው እንዳይረክሱ በማለት ወደ አገረ ገዢው ግቢ ውስጥ አልገቡም። ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጣና “በዚህ ሰው ላይ ያቀረባችሁት ክስ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ይህ ሰው ክፉ አድራጊ ባይሆን ኖሮ ለአንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” ሲሉ መለሱለት። ጲላጦስም “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም “እኛ ሰውን ለመግደል አልተፈቀደልንም” አሉት። ይህም የሆነው ኢየሱስ በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ጲላጦስ እንደገና ወደ ግቢው ተመልሶ ገባ፤ ኢየሱስንም ጠርቶ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን? ወይስ ሌሎች ይህን ስለ እኔ ነግረውሃል?” አለው። ጲላጦስም “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? አንተን ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ ወገኖችህና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ምንድን ነው ያደረግኸው?” አለው። ኢየሱስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ በአይሁድ ባለሥልጣኖች እጅ እንዳልወድቅ ሎሌዎቼ በተዋጉልኝ ነበር፤ መንግሥቴ ግን ከዚህ ዓለም አይደለችም” ሲል መለሰ። ጲላጦስም “ታዲያ፥ አንተ ንጉሥ ነኻ?” አለው። ኢየሱስም “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንኩ አንተ ትላለህ፤ እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ልመሰክር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ቃሌን ይሰማል” ሲል መለሰ። ጲላጦስም “እውነት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ እንደገና ወደ አይሁድ ወጣና እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤
ዮሐንስ 18:28-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም እንዳይረክሱ፥ ይልቁንም የፋሲካን በግ እንዲበሉ በማለት ወደ ገዢው ግቢ አልገቡም። ስለዚህም ጲላጦስ ወደ ውጭ፥ ወደ እነርሱ ወጥቶ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ምን ዓይነት ክስ ነው አላቸው?” አላቸው። እነርሱም መልሰው “ይህ ሰው ክፉ አድራጊ ባይሆን ለአንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” አሉት። ጲላጦስም “እናንተ ወስዳችሁ በሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም “እኛስ ማንንም ለመግደል አልተፈቀደልንም፤” አሉት፤ ይህም ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት እንደሚሞት ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነብር። ጲላጦስም እንደገና ወደ ገዢው ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህ?” አለው። ጲላጦስ መልሶ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ ነገር ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” አለው። ጲላጦስም “እንግዲያውስ ንጉሥ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ ንጉሥ እንደሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ተወልጃለሁ፤ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” አለው። ጲላጦስ “እውነት ምንድነው?” አለው። ይህንንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጣና “እኔስ አንዲት በደል እንኳን አላገኘሁበትም።