ማቴዎስ 22:34-40
ማቴዎስ 22:34-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ። ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው “መምህር ሆይ! ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።’ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም ‘ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ፤’ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።”
ማቴዎስ 22:34-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ሰምተው፣ ፈሪሳውያን በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ከእነርሱም አንድ የኦሪት ሕግ ዐዋቂ፣ ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትእዛዝ ነው?” እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዞች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።”
ማቴዎስ 22:34-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ። ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው፦ መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።
ማቴዎስ 22:34-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ሰዱቃውያንን መልስ አሳጥቶ ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ ፈሪሳውያን በአንድነት ተሰበሰቡ። ከእነርሱም አንድ የሕግ መምህር፥ ኢየሱስን ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “መምህር ሆይ! ከሕግ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታ አምላክህን በሙሉ ልብህ፥ በሙሉ ነፍስህ፥ በሙሉ ሐሳብህ ውደድ፤ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ይህ ነው። ይህንንም የሚመስለው ሁለተኛው ትእዛዝ፥ ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ የሚለው ነው። የሕግና የነቢያት ትምህርት ሁሉ የተመሠረቱት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዞች ላይ ነው።”
ማቴዎስ 22:34-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “መምህር ሆይ! ከሕግ ማንኛይቱ ትእዛዝ ትበልጣለች?” እርሱም እንዲህ አለው “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ።’ ታላቂቱና የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርሷም ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤’ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕግና ነቢያት ሁሉ ተንጠልጥለዋል።”