ማርቆስ 8:1-21
ማርቆስ 8:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያ ወራት ደግሞ ብዙ ሕዝብ ነበረ፤ የሚበሉትም ስለሌላቸው ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ “ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና፥ ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል?” ብለው መለሱለት። እርሱም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ሰባት” አሉት። ሕዝቡም በምድር እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፤ ቈርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ለሕዝቡም አቀረቡ። ጥቂትም ትንሽ ዓሣ ነበራቸው፤ ባረከውም፤ ይህንም ደግሞ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ። በሉም፤ ጠገቡም፤ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ። የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ፤ አሰናበታቸውም። ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ። ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር። በመንፈሱም እጅግ ቃተተና “ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም፤” አለ። ትቶአቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ማዶ ሄደ። እንጀራ መያዝም ረሱ፤ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም። እርሱም “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። እርስ በርሳቸውም “እንጀራ ስለሌለን ይሆናል፤” ብለው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው “እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን? ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዐይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ” እነርሱም “ዐሥራ ሁለት፤” አሉት። ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም “ሰባት” አሉት። “ገና አላስተዋላችሁምን?” አላቸው።
ማርቆስ 8:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያ ጊዜ፣ እንደ ገና ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። የሚበሉት ምንም ምግብ ስላልነበራቸው ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ከእኔ ጋራ ሦስት ቀን ስለ ቈዩና የሚበሉትም ስለሌላቸው ለእነዚህ ሰዎች ዐዝንላቸዋለሁ፤ እንዲህ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ብሰድዳቸው አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ስለ ሆኑ በመንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ።” ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፣ “በዚህ ምድረ በዳ እነዚህን ለመመገብ የሚያስችል እንጀራ ከወዴት ይገኛል?” አሉት። እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት። እርሱም፣ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ ዐደሉት። እንዲሁም ትንንሽ ዓሣዎች ነበሯቸው፤ እርሱም ዓሣዎቹን ባርኮ እንዲያድሏቸው አዘዘ። ሕዝቡም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። በዚያም አራት ሺሕ ያህል ሰዎች ነበሩ፤ ካሰናበታቸውም በኋላ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ጀልባ ገብቶ ዳልማኑታ ወደ ተባለ ስፍራ ሄደ። ፈሪሳውያንም ወጥተው ከኢየሱስ ጋራ ይከራከሩ ጀመር። ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳይ ጠየቁት። እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፣ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም!” አለ። ከዚያም ትቷቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ። ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ፣ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት የምትነጋገሩት ስለ ምንድን ነው? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? ዐምስቱን እንጀራ ለዐምስት ሺሕ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፣ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺሕ በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት። እርሱም፣ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን?” አላቸው።
ማርቆስ 8:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያ ወራት ደግሞ ብዙ ሕዝብ ነበረ የሚበሉትም ስለሌላቸው ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፦ ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፦ በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት። እርሱም፦ ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው፥ እነርሱም፦ ሰባት አሉት። ሕዝቡም በምድር እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፥ ቈርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ለሕዝቡም አቀረቡ። ጥቂትም ትንሽ ዓሣ ነበራቸው፤ ባረከውም ይህንም ደግሞ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ። በሉም ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ። የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ። አሰናበታቸውም። ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ። ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር። በመንፈሱም እጅግ ቃተተና፦ ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ። ትቶአቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ማዶ ሄደ። እንጀራ መያዝም ረሱ፥ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም። እርሱም፦ ተጠንቀቁ፥ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው። እርስ በርሳቸውም፦ እንጀራ ስለሌለን ይሆናል ብለው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን? ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዓይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እነርሱም፦ አሥራ ሁለት አሉት። ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም፦ ሰባት አሉት። ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው።
ማርቆስ 8:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ሰሞን እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ የሚበሉትም አልነበራቸውም፤ ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “እነዚህ ሰዎች እነሆ፥ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ቈይተዋል፤ ምንም የሚበሉት ምግብ ስለሌላቸው እራራላቸዋለሁ፤ እንዲሁ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይደክማሉ፤ እንዲያውም ከእነርሱ አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ናቸው።” ደቀ መዛሙርቱም፦ “ታዲያ፥ በዚህ በረሓ ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች የሚበቃ እንጀራ ማግኘት ማን ይችላል?” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ሰባት እንጀራ አለን፤” አሉት። እርሱም በመሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱንም እንጀራ ይዞ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አቀረቡ። ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎችም ነበሩአቸው፤ ስለ ዓሣዎቹም እግዚአብሔርን ካመሰገነ በኋላ ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። ሰዎቹም ሁሉ በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቊርስራሽ ሰብስበው ሰባት ትላልቅ መሶብ ሙሉ አነሡ። የተመገቡት ሰዎች አራት ሺህ ያኽል ነበሩ፤ ኢየሱስ እነርሱን አሰናበታቸው። ከዚያ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ሆኖ ወደ ዳልማኑታ አውራጃ ሄደ። ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ መጡና ከእርሱ ጋር መከራከር ጀመሩ፤ ሊፈትኑትም አስበው ከሰማይ አንድ ተአምር እንዲያሳያቸው ጠየቁት። ኢየሱስ በመንፈሱ በመቃተት፦ “የዚህ ዘመን ትውልድ ተአምር እንዲደረግለት ስለምን ይፈልጋል? በእውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ተአምር አይደረግለትም!” አላቸው። ትቶአቸውም እንደገና በጀልባ ሆኖ ወደ ማዶ ተሻገረ። ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ በጀልባው ውስጥ ከአንድ እንጀራ በቀር ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠንቀቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም “ይህን ማለቱ፥ ምናልባት እንጀራ ስለሌለን ይሆናል፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም ይህንኑ ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እንጀራ ስለሌለን ነው ብላችሁ ስለምን ታስባላችሁ? ገና ምንም የማታስተውሉና የማይገባችሁ ናችሁን? ልባችሁስ ገና እንደ ደነዘዘ ነውን? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮስ እያላችሁ አትሰሙምን? እንዴትስ ትዝ አይላችሁም? ለመሆኑ አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” እነርሱም “ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ” አሉት። “እንዲሁም ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰባት መሶብ ሙሉ” አሉት። እርሱም “ታዲያ፥ ገና አታስተውሉምን?” አላቸው።
ማርቆስ 8:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜ፥ እንደገና ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። የሚበሉት ምንም ምግብ ስላልነበራቸው ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ስለቆዩና የሚበሉትም ስለ ሌላቸው እነዚህ ሰዎች ያሳዝኑኛል፤ እንዲህ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ስለ ሆኑ በመንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ። ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፥ “በዚህ ምድረ በዳ እነዚህን ለመመገብ የሚያስችል እንጀራ ከወዴት ይገኛል?” አሉት። እርሱም፥ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። እርሱም፥ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቆርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አደሉት። እንዲሁም ትንንሽ ዓሣዎች ነበሯቸው፤ እርሱም ዓሣዎቹን ባርኮ እንዲያድሏቸው አዘዘ። ሕዝቡም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀመዛሙርቱ የተረፈውን ቁርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። በዚያም አራት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱንም አሰናበታቸው። ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ዳልማኑታ ወደ ተባለ ስፍራ ሄደ። ፈሪሳውያንም ወጥተው ከኢየሱስ ጋር ይከራከሩ ጀመር። ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፥ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም” አለ። ከዚያም ትቷቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ። ደቀመዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለረሱ፥ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም፥ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፥ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፥ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺህ በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። እርሱም፥ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን” አላቸው።