የማርቆስ ወንጌል 8:1-21

የማርቆስ ወንጌል 8:1-21 መቅካእኤ

በዚያን ጊዜ፥ እንደገና ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። የሚበሉት ምንም ምግብ ስላልነበራቸው ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ስለቆዩና የሚበሉትም ስለ ሌላቸው እነዚህ ሰዎች ያሳዝኑኛል፤ እንዲህ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ስለ ሆኑ በመንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ። ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፥ “በዚህ ምድረ በዳ እነዚህን ለመመገብ የሚያስችል እንጀራ ከወዴት ይገኛል?” አሉት። እርሱም፥ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። እርሱም፥ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቆርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አደሉት። እንዲሁም ትንንሽ ዓሣዎች ነበሯቸው፤ እርሱም ዓሣዎቹን ባርኮ እንዲያድሏቸው አዘዘ። ሕዝቡም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀመዛሙርቱ የተረፈውን ቁርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። በዚያም አራት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱንም አሰናበታቸው። ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ዳልማኑታ ወደ ተባለ ስፍራ ሄደ። ፈሪሳውያንም ወጥተው ከኢየሱስ ጋር ይከራከሩ ጀመር። ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፥ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም” አለ። ከዚያም ትቷቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ። ደቀመዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለረሱ፥ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም፥ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፥ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፥ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺህ በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። እርሱም፥ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን” አላቸው።