የማርቆስ ወንጌል 8:1-21

የማርቆስ ወንጌል 8:1-21 አማ05

በዚያን ሰሞን እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ የሚበሉትም አልነበራቸውም፤ ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “እነዚህ ሰዎች እነሆ፥ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ቈይተዋል፤ ምንም የሚበሉት ምግብ ስለሌላቸው እራራላቸዋለሁ፤ እንዲሁ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይደክማሉ፤ እንዲያውም ከእነርሱ አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ናቸው።” ደቀ መዛሙርቱም፦ “ታዲያ፥ በዚህ በረሓ ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች የሚበቃ እንጀራ ማግኘት ማን ይችላል?” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ሰባት እንጀራ አለን፤” አሉት። እርሱም በመሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱንም እንጀራ ይዞ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አቀረቡ። ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎችም ነበሩአቸው፤ ስለ ዓሣዎቹም እግዚአብሔርን ካመሰገነ በኋላ ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። ሰዎቹም ሁሉ በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቊርስራሽ ሰብስበው ሰባት ትላልቅ መሶብ ሙሉ አነሡ። የተመገቡት ሰዎች አራት ሺህ ያኽል ነበሩ፤ ኢየሱስ እነርሱን አሰናበታቸው። ከዚያ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ሆኖ ወደ ዳልማኑታ አውራጃ ሄደ። ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ መጡና ከእርሱ ጋር መከራከር ጀመሩ፤ ሊፈትኑትም አስበው ከሰማይ አንድ ተአምር እንዲያሳያቸው ጠየቁት። ኢየሱስ በመንፈሱ በመቃተት፦ “የዚህ ዘመን ትውልድ ተአምር እንዲደረግለት ስለምን ይፈልጋል? በእውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ተአምር አይደረግለትም!” አላቸው። ትቶአቸውም እንደገና በጀልባ ሆኖ ወደ ማዶ ተሻገረ። ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ በጀልባው ውስጥ ከአንድ እንጀራ በቀር ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠንቀቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም “ይህን ማለቱ፥ ምናልባት እንጀራ ስለሌለን ይሆናል፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም ይህንኑ ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እንጀራ ስለሌለን ነው ብላችሁ ስለምን ታስባላችሁ? ገና ምንም የማታስተውሉና የማይገባችሁ ናችሁን? ልባችሁስ ገና እንደ ደነዘዘ ነውን? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮስ እያላችሁ አትሰሙምን? እንዴትስ ትዝ አይላችሁም? ለመሆኑ አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” እነርሱም “ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ” አሉት። “እንዲሁም ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰባት መሶብ ሙሉ” አሉት። እርሱም “ታዲያ፥ ገና አታስተውሉምን?” አላቸው።