መዝሙር 130:1-8
መዝሙር 130:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥልቅ ወደ አንተ እጮኻለሁ። ጌታ ሆይ፤ ድምፄን ስማ፤ ጆሮዎችህ የልመናዬን ቃል፣ የሚያዳምጡ ይሁኑ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል? ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ፤ ስለዚህም ልትፈራ ይገባሃል። እግዚአብሔርን ደጅ እጠናለሁ፤ ነፍሴም በትዕግሥት ትጠብቀዋለች፤ በቃሉም ተስፋ አደርጋለሁ። ዘብ ዐዳሪ ንጋትን ከሚጠባበቅ ይልቅ፣ አዎን፤ ዘብ ዐዳሪ ንጋትን ከሚጠባበቅ ይልቅ፣ ነፍሴ ጌታን ትጠባበቃለች። በእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፣ በርሱም ዘንድ ማዳን አለና፣ እስራኤል ሆይ፤ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርግ። እርሱም እስራኤልን፣ ከኀጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።
መዝሙር 130:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! ከጥልቅ ሐዘን የተነሣ ወደ አንተ እጮኻለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ልመናዬን ስማ! ምሕረትህን ፈልጌ ስጮኽም አድምጠኝ! ኃጢአታችንን ብትከታተል ማን ከፍርድ ሊያመልጥ ይችላል? ነገር ግን አንተን እንድናከብርህ ኃጢአታችንን ይቅር ትልልናለህ። እግዚአብሔርን በናፍቆት እጠባበቃለሁ፤ በቃሉም እታመናለሁ። ንጋትን ከሚጠባበቁ ጠባቂዎች ይልቅ እኔ እግዚአብሔርን በናፍቆት እጠባበቃለሁ። እስራኤል ሆይ! ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ስለ ሆነና ሰዎችንም የማዳን ኀይል ያለው ስለ ሆነ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ። እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን ከኃጢአታቸው ሁሉ ያድናቸዋል።
መዝሙር 130:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ አንተን ከጥልቅ ጠራሁህ። አቤቱ፥ ድምፄን ስማ፥ ጆሮህ የልመናዬን ቃል ያድምጥ። አቤቱ፥ ኃጢአትን ብትይዝ፥ አቤቱ፥ ማን ይቆማል? ይቅርታ በአንተ ዘንድ ነውና። አቤቱ ተስፋ አደረግሁ፥ ነፍሴ ጠበቀች፥ በቃሉ ታመንኩ። ማለዳን ከሚጠብቁ የሌሊት ጠባቂዎች ይልቅ፥ ነፍሴ ጌታን ትጠብቃለች፥ ማለዳን ከሚጠብቁ ጠባቂዎች ይልቅ። ከጌታ ጋር ጽኑ ፍቅር፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን አለና እስራኤል በጌታ ይታመን። እርሱም እስራኤልን ከበደሉ ሁሉ ያድነዋል።