YouVersion Logo
Search Icon

ኢሳይያስ 26

26
የምስጋና መዝሙር
1በዚያ ቀን ይህ መዝሙር በይሁዳ ምድር ይዘመራል፤
ብርቱ ከተማ አለችን፤
አምላካችን ቅጥሮቿንና ምሽጎቿን፣
ለድነት አድርጓል።
2በእምነቱ የጸና
ጻድቅ የሆነ ሕዝብ ይገባ ዘንድ፣
በሮቿን ክፈቱ።
3በአንተ ላይ ታምናለችና፣
በአንተ የምትደገፈውን ነፍስ
ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።
4እግዚአብሔር ለዘላለም ታመኑ፤
ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም ዐለት ነውና።
5በከፍታ የሚኖሩትን ዝቅ ዝቅ ያደርጋል፤
ከፍ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፤
ወደ ምድር ይጥላታል፤
ከትቢያም ጋራ ይደባልቃታል።
6እግር፣
የተጨቋኞች እግር፣
የድኾች ኮቴ ይረግጣታል።
7የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤
አንተ ቅን የሆንህ ሆይ፤
የጻድቃንን መንገድ ታቃናለህ።
8 እግዚአብሔር ሆይ፤ በሕግህ#26፥8 ወይም፣ በፍርድህ ተብሎ መተርጐም ይችላል። ጐዳና በመሄድ፣
አንተን ተስፋ አድርገናል፤
ስምህና ዝናህ፣
የልባችን ምኞት ነው።
9ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፤
መንፈሴም በውስጤ ትፈልግሃለች።
ፍርድህ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ፣
የዓለም ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ።
10ክፉዎች ርኅራኄ ቢደረግላቸው እንኳ፣
ጽድቅን አይማሩም፤
በቅንነት ምድር እንኳ ክፋትን ያደርጋሉ፤
እግዚአብሔርንም ግርማ አያስተውሉም።
11 እግዚአብሔር ሆይ፤ ክንድህ ከፍ ከፍ ብሏል፤
እነርሱ ግን አላስተዋሉም፤
ለሕዝብህ ያለህን ቅናት ይዩ፤ ይፈሩም፤
ለጠላቶችህም የተዘጋጀው እሳት ይብላቸው።
12 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰላምን መሠረትህልን፤
የሠራነውንም ሁሉ አንተ አከናወንህልን።
13 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤
ከአንተ ሌላ ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤
እኛ ግን የአንተን ስም ብቻ እናከብራለን።
14እነርሱ ሞተዋል፤ ከእንግዲህ በሕይወት አይኖሩም፤
መንፈሳቸው ተነሥቶ አይመጣም።
አንተ ቀጣሃቸው፤ አጠፋሃቸው፤
መታሰቢያቸውንም ሁሉ ደመሰስህ።
15 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብን አበዛህ፤
ሕዝብን አበዛህ።
ክብሩን ለራስህ አደረግህ፤
የምድሪቱንም ወሰን ሁሉ አሰፋህ።
16 እግዚአብሔር ሆይ፤ በተጨነቁ ጊዜ ወደ አንተ መጡ፤
በገሠጽሃቸውም ጊዜ፣
በለኆሳስ ድምፅ ይጸልያሉ#26፥16 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም።
17 እግዚአብሔር ሆይ፤ የፀነሰች ሴት ልትወልድ ስትል፣
በምጥ እንደምትጨነቅና እንደምትጮኽ፣
እኛም በፊትህ እንዲሁ ሆነናል።
18አረገዝን በምጥም ተጨነቅን፤
ነገር ግን ነፋስን ወለድን፤
ለምድርም ድነትን አላመጣንም፤
የዓለምን ሕዝብ አልወለድንም።
19ነገር ግን ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤
በድናቸውም ይነሣል።
እናንተ በዐፈር ውስጥ የምትኖሩ፣
ተነሡ፤ በደስታም ዘምሩ።
ጠልህ እንደ ንጋት ጠል ነው፤
ምድር ሙታንን ትወልዳለች።
20ሕዝቤ ሆይ፤ ሂድ ወደ ቤትህ ግባ፤
በርህን ከኋላህ ዝጋ፤
ቍጣው እስኪያልፍ ድረስ፣
ለጥቂት ቀን ተሸሸግ።
21በምድር ላይ የሚኖረውን ሕዝብ ስለ ኀጢአቱ ለመቅጣት፣
እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያው ወጥቶ ይመጣል፤
ምድር በላይዋ የፈሰሰውን ደም ትገልጣለች፤
የተገደሉትንም ከእንግዲህ አትሸሽግም።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 26: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ኢሳይያስ 26