ኢሳይያስ 27
27
የእስራኤል ዐርነት መውጣት
1በዚያ ቀን እግዚአብሔር፣
ተወርዋሪውን እባብ ሌዋታንን፣
የሚጠቀለለውን ዘንዶ ሌዋታንን
በብርቱ፣ በታላቁና በኀይለኛ ሰይፍ ይቀጣዋል፤
የባሕሩንም ግዙፍ አውሬ ይቈራርጠዋል።
2በዚያ ቀን እንዲህ ይባላል፤
“ለመልካሙ የወይን ቦታ ዘምሩለት፤
3እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፤
ዘወትር ውሃ አጠጣዋለሁ፤
ስለዚህ ማንም አይጐዳውም፣
ቀንና ሌሊት እጠብቀዋለሁ፤
4እኔ አልቈጣም።
እሾኽና ኵርንችት ምነው በተነሡብኝ!
ለውጊያ በወጣሁባቸው፣
አንድ ላይ ባቃጠልኋቸው!
5አለዚያ ይምጡና መሸሸጊያቸው ያድርጉኝ፤
ከእኔ ጋራ ሰላም ይፍጠሩ፤
አዎን፤ ከእኔ ጋራ ሰላም ያድርጉ።”
6በሚመጡት ቀናት ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፤
እስራኤልም ያቈጠቍጣል፣ ያብባልም፤
በፍሬአቸውም ምድርን ሁሉ ይሞላሉ።
7የመቷትን እንደ መታቸው፣
እግዚአብሔር እርሷንስ መታትን?
የገደሏትን እንደ ገደላቸው፣
እርሷስ ተገደለችን?
8በጦርነትና በስደት ተፋለምሃት#27፥8 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም።፤
የምሥራቅ ነፋስ እንደሚነፍስበት ቀን፣
በብርቱ ዐውሎ ነፋስ አሳደድሃት።
9ያዕቆብ የመሠዊያ ድንጋዮችን፣
እንደ ኖራ ድንጋይ ፈጭቶ ሲያደቅቃቸው፣
የአሼራን ዐምድና የዕጣን መሠዊያዎችን፣
ከቦታቸው ነቅሎ ሲጥል፣
በዚያ ጊዜ በደሉ ይሰረይለታል፤
ይህም ኀጢአቱ የመወገዱ ሙሉ ፍሬ ይሆናል።
10የተመሸገባት ከተማ ባዶዋን ቀርታለች፤
እንደ ምድረ በዳም የተተወች ስፍራ ሆናለች፤
ጥጆች በዚያ ይሰማራሉ፤
እዚያም ይተኛሉ፤
ቅርንጫፎቿንም ልጠው ይበላሉ።
11ጫፎቿ ሲደርቁ ይሰበራሉ፤
ሴቶችም መጥተው ይማግዷቸዋል።
ማስተዋል የሌለው ሕዝብ ስለ ሆነ፣
ፈጣሪው አይራራለትም፤
ያበጀውም አይምረውም።
12በዚያ ቀን ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ እስከ ግብጽ ደረቅ ወንዝ፣ እግዚአብሔር እህሉን ይወቃል፤ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፤ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ። 13በዚያ ቀን ታላቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦር የጠፉትና በግብጽ የተሰደዱትም መጥተው፣ በተቀደሰው ተራራ በኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ያመልካሉ።
Currently Selected:
ኢሳይያስ 27: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.