ማቴዎስ 18
18
በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?
18፥1-5 ተጓ ምብ – ማር 9፥33-37፤ ሉቃ 9፥46-48
1በዚያ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።
2ኢየሱስ አንድ ሕፃን ወደ ራሱ ጠርቶ በመካከላቸው አቆመና እንዲህ አላቸው፤ 3“እውነት እላችኋለሁ፤ ካልተለወጣችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። 4ስለዚህ በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ፣ እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው። 5ማንም እንደዚህ ያለውን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል።
6 “ነገር ግን ማንም በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል፣ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥሎ ቢሰጥም ይሻለዋል። 7ይህች ዓለም የመሰናክል ምክንያት በመሆኗ ወዮላት! መሰናክል መምጣቱ አይቀርምና፤ ነገር ግን የመሰናክሉ ምክንያት ለሚሆነው ሰው ወዮለት! 8እጅህ ወይም እግርህ ለመሰናክል ምክንያት ቢሆንብህ፣ ቈርጠህ ጣለው፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል፣ ዐንካሳ ወይም ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። 9እንዲሁም ዐይንህ ለመሰናክል ምክንያት ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።
የጠፋው በግ ምሳሌ
18፥12-14 ተጓ ምብ – ሉቃ 15፥4-7
10 “ከእነዚህ ከታናናሾች መካከል አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ እላችኋለሁና፤ በሰማይ ያሉት መላእክታቸው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ሁልጊዜ ያያሉ፤ [11ምክንያቱም የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነው።]#18፥11 አንዳንድ ትርጕሞች በሉቃ 19፥10 ያሉትን ቃላት ይጨምራሉ።
12 “እስኪ ንገሩኝ፤ አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት፣ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ለመፈለግ አይሄድምን? 13እውነት እላችኋለሁ፤ የጠፋውን በግ ሲያገኝ፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በዚያ በተገኘው ደስ ይለዋል። 14እንደዚሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱ እንኳ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም።
ስለ መቀያየም
15 “ወንድምህ # 18፥15 የግሪኩ ቃል ወንድም ወይም እኅት የሚለው ቃል ዐብሮ ላለ ደቀ መዝሙርም ብሎ ሊያመለክት ይችላል። በቍጥር 21 እና 35 ላለውም ተመሳሳይ ነው። ቢበድልህ#18፥15 አንዳንድ ቅጆች ቢበድል ወይም ኀጢአት ቢሠራ ይላሉ። ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን እንደ ገና የራስህ ታደርገዋለህ። 16ባይሰማህ ግን፣ ነገር ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ስለሚጸና፣ አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ አነጋግረው። 17እነርሱን ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ፣ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቍጠረው።
18 “እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ያሰራችሁት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታችሁት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።
19 “ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ላይ ሁለት ሆናችሁ ስለ ምንም ነገር በመስማማት ብትጠይቁ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል፤ 20ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁና።”
ይቅርታ ስለ ማድረግ
21በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው።
22ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” አለው።
23 “ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ፣ በባሪያዎቹ እጅ የነበረውን ሒሳብ ለመተሳሰብ የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች። 24ሒሳቡን ማጣራት እንደ ጀመረም ዐሥር ሺሕ ታላንት#18፥24 ታላንት ማለት የአንድ ቀን ሠራተኛ የኻያ ዓመታት ደመወዝን የሚያህል ነው። ዕዳ ያለበትን አንድ አገልጋይ አቀረቡለት። 25አገልጋዩም ያለበትን ዕዳ መክፈል ስላቃተው እርሱ ራሱ፣ ሚስቱ፣ ልጆቹና ንብረቱ ሁሉ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ።
26 “በዚህ ጊዜ ባሪያው እግሩ ላይ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። 27ጌታውም ዐዘነለትና ባሪያውን ማረው፤ ዕዳውንም ትቶለት አሰናበተው።
28 “ያ ባሪያ ከጌታው ፊት እንደ ወጣ አንድ መቶ ዲናር # 18፥28 ዲናር ማለት የቀን ሠራተኛ የአንድ ቀን ክፍያ ነው። የርሱ ዕዳ ያለበትን አገልጋይ ባልንጀራውን አግኝቶ ዕንቅ አድርጎ በመያዝ፣ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ!’ አለው።
29 “ባልንጀራው አገልጋይም ከፊቱ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ለመነው።
30 “ነገር ግን ሊታገሠው ፈቃደኛ ስላልነበረ፣ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍለው ድረስ ወህኒ ቤት አስገባው። 31የሆነውን ነገር ያዩ ሌሎች አገልጋዮችም በጣም ዐዘኑ፤ ሄደውም ሁኔታውን በሙሉ ለጌታቸው ነገሩት።
32 “በዚህ ጊዜ ጌታው ባሪያውን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፤ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤ 33እኔ እንደ ማርሁህ አንተም ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?’ 34በቍጣም ያለበትን ዕዳ ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ ለአሳሪዎች አሳልፎ ሰጠው።
35 “ስለዚህ እያንዳንዳችሁ ወንድሞቻችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፣ የሰማዩ አባቴም እንደዚሁ ያደርግባችኋል።”
Currently Selected:
ማቴዎስ 18: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.